በቃሊቲ እስር ቤት ህይወቱ ያለፈ አንድ ኬንያዊ አስከሬኑ ወደ አገሩ ተመለሰ

ኢሳት (ታህሳስ 7 ፥2009)

በቃሊቲ እስር ቤት ህይወቱ ያለፈ አንድ ኬንያዊ የቴክኖሎጂ ምህንድስና ባለሙያ አስከሬኑ ወደ ኬንያ መመለሱን ቤተሰቦቹ ለመገናኛ ብዙሃን አስታወቁ።

የሁለት ሴት ልጆች አባት የነበረው ዛክ ሚሪዩኪ ባለፈው አመት በስልክ የመሰረተ ልማት አገልግሎት ላይ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ በጅጅጋ ከተማ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት መዛወሩ ታውቋል።

ሟቹ ኬንያዊ ከሌላ አንድ ባልደርባው ጋር በመሆን ኢንተርሳት በተባለ ኩባንያ ለደንበኞች የሳተላይት የመገናኛ ቁሳቁሶችን ለመዘርጋት ተልኮ እንደነበር ኩባንያው ገልጿል።

ይሁንና የቴክኖሎጂ ኩባንያው ሁለቱ ኬንያውያን ባለሙያዎች አገልግሎት ለማን ይሰጡ እንደነበር የገለጸው ነገር የሌም፣ በቃሊቲ እስር ቤት እያለ ህይወቱ ያለፈው በሃገሪቱ መነጋገሪያ መሆኑ ለመረዳት ተችሏል።

የቴክኖሎጂ ምህንስና ባለሙያ የነበረው ዛክ ሚሪዩኪ በአዲስ አበባ ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወንጀለኛ ፍርድቤት የቀረበበት ክስ በመታየት ላይ እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።

ተከሳሹ በቃሊቲ እስር ቤት እያለ ለበርካታ ወራቶች በማጅራት ገትር በሽታ ይታመም የነበረ ቢሆንም፣ በቂ ህክምና ሳያገኝ መቆየቱን መጽሄቱ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አመልክቷል።

የሟቹ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ የአስከሬኑ ከአራት ቀን በፊት ወደ ኬንያ መሄዱንና ለቤተሰቦቹ መስጠቱን ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና በኬንያ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በድርጊቱ የተሰማቸውን ቁጣ እየገለጹ ይገኛል። ከሟች ጋር በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ጃሪክ ሙጎ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኝ መሆኑም ታውቋል።

የኬንያውን ሞት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሆነ የኬንያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ የሌም፣ በተለያዩ ጊዜያት ቁጥራቸው የማይታወቅ እስረኞች በቃሊቲና በሌሎች የክልልና የፌዴራል እስር ቤቶች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንደሚሞቱ ይገልጻሉ።