ኢሳት (ጳጉሜ 1 ፥ 2008)
በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ የእስር ቤቱ የጸጥታ ሃይሎች በእስረኞች ላይ የጅምላ የተኩስ እርምጃን ሲወስዱ እንደነበር በእለቱ በእስር ቤቱ ጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ የጸጥታ ባልደርባ ገለጸ።
ለደህንነቱ ሲል ስሙን ያልገለጸው ይኸው የቂሊንጦ እስር ቤት ጠባቂ በ20 ደቂቃ አምስት እስረኞች በኢላማ ተኩስ ተገድለው መመልከቱን አዲስ አበባ ውስጥ ለሚታተመው አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ አስረድቷል።
መሳሪያን ሳይታጠቅ በእለቱ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር የገለጸው የቂሊንጦ እስር ቤቱ የጸጥታ ባልደርባ እሱን ጨምሮ ሌሎች ያልታጠቁ የጸጥታ አባላት በእለቱ እስረኞች ሊጠይቁ የመጡ ሰዎችን እንዲመለሱ ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበር ይፋ አድርጓል።
በእስር ቤቱ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት እስረኞች ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ያወሳው የጸጥታ ባልደልባ ከቅዳሜ ጀምሮ እሱና ሌሎች ባልደርቦች ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት እንዳይገቡ መደረጉን አክሎ አስረድቷል።
በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ስር ይተዳደር የነበረው የቂሊንጦ እስር ቤት፣ በአሁኑ ወቅት በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር እንዲሆን መደረጉን አደጋው በደረሰ ወቅት በስራ ላይ የነበረው የጸጥታ ባልደርባ አመልክቷል።
በተኩስ እርምጃ የተገደሉ 18 እስረኞችን ከእስር ቤት ለማውጣት ተሳትፎ እንደነበረው የገለጸው እማኝ አንድ እስረኛ ብቻ በእሳት ቃጠሎ መሞቱን ገልጿል።
መንግስት በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ 21 እስረኞች በእሳት ጢስ በመታፈንና በመረጋገጥ መሞታቸውን መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና በዕለቱ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ባልደርባ አንድ እስረኛ ብቻ በእሳት አደጋ መሞቱን አረጋግጦ የታጠቁ የቂሊንጦ የጸጥታ ሃይሎች የጅምላ የተኩስ እርምጃ መውሰዳቸውን ለህዝብ ይፋ እንዲሆን በፈለገው እማኝነት ለመጽሄቱ አስረድቷል።
የቂሊንጦው እስር ቤት እስከ ማክሰኞች ድረስ ከባድ መሳሪያን በታጠቁ የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ጥበቃ እየተደረገለት እንደሚገኝና ማንም ሰው ወደ ስፍራው እንዳይጠጋ እገዳ መጣሉን ለመረዳት ተችሏል።
በእስር ቤቱ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች የደህንነታቸው ሁኔታ ሊረጋገጥ አለመቻሉ ታውቋል።