በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሁለት እስረኞች በድብደባ ሕይወታቸው አለፈ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010)በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙ ሁለት እስረኞች በድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን የሟቾቹ አባሪዎች ዛሬ ለፍርድ ቤት አስታወቁ።

ከሟቾቹ አንዱ ለደህንነቴ እሰጋለሁ እስር ቤት ይቀየርልኝ ብሎ ለፍርድ ቤት ካመልከተ በኋላ መገደሉም ይፋ ሆኗል።

በድብደባ ሕይወታቸው ያለፈው አለማዬ ዋቄ ማሞና መሀመድ ጫኔ የተባሉ እስረኞች ሲሆኑ የቂሊንጦ ወህኒ ቤትን በማቃጠል ተወንጅለው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በመከታተል ላይ እንደነበሩም ታውቋል።

ዛሬ ጥቅምት 15/2010 አዲስ አበባ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት የነበረውን ውሎ ተከታትሎ በማህበራዊ ገጹ ዘገባውን ያቀረበው ጌታቸው ሽፈራው ቀደም ሲል በዚሁ ወህኒ ቤት ድብደባ የተፈጸመባቸውን አግባው ሰጠኝ፣ዘመነ ጌቴና ለገሰ ወልደሃናን አስታውሷል።

1ኛው ተከሳሽ ብስራት አበራ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው ግድያው የተፈጸመው በአደባባይ ሲሆን 15ኛውን ተከሳሽ አለማዬ ዋቆ ማሞን ልቡን ረግጠው እንደገደሉም ዛሬ ጥቅምት 15/2010 አዲስ አበባ ለተሰየመው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት አስታውቋል።

1ኛው ተከሳሽ ብስራት አበራ እንደተናገረውና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በማህበራዊ ገጹ እንዳሰፈረው ግድያው የተፈጸመው የቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሃላፊ ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ ባለበት ሲሆን በሌሎቹ ተከሳሾችም ላይ ድብደባ ተፈጽሟል።

በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ቃጠሎ በማስነሳት በሚል ከተከሰሱት ሁለቱ በድብደባ መገደላቸውን ለፍርድ ቤቱ የገለጸው 1ኛው ተከሳሽ ብስራት አበራ ሟች አለማዬ ዋቄ ለደህንነቱ እንደሚሰጋና እስር ቤት እንዲቀይሩለት ለዚሁ ፍርድ ቤት አመልክቶ እንደነበርም አስታውቋል።

በሁለቱ ተከሳሾች ላይ በድብደባ ግድያ መፈጸሙን በችሎት ለዳኞቹ የተናገረው 1ኛው ተከሳሽ ብስራት አበራ እርሱም ይህንን ወንጀል በማጋለጡ የእርሱም ሕይወት ለአደጋ መጋለጡን በመግለጽ ወደ ገዳዮች አትመልሱኝ ሌላ እስር ቤት ቀይሩኝ ብሎ ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከተም ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ምንም ማድረግ አልችልም በማለቱ ተከሳሽ በፖሊስ በሰንሰለት ታስሮ መወሰዱም ተመልክቷል።

በተለያዩ ጉዳዮች ተከሰው ወህኒ ቤት ውስጥ ግድያ ከተፈጸመባቸው ውስጥ በህዳር ወር 1998 በጥይት ከተመታ በኋላ ሚኒሊክ ሆስፒታል ሕይወቱ ያለፈው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ተማሪ አለማየሁ ገርባ ተጠቅሷል።

በዚሁ አመት ወህኒ ቤት ውስጥ ሞባይል ስልክ አስገብተሃል በሚል ጋዲሳ ሒርጳሳ የተባለ የፖለቲካ እስረኛም በቃሊቲ ወህኒ ቤት መገደሉን ማስታወስ ተችሏል።

ታህሳስ 27 2007 በዝዋይ ወህኒ ቤት ኮለኔል ደምሰው አንተነህና ኮለኔል አለሙ ጌትነት በጥይት መደብደባቸው ይታወሳል።

ሆኖም እነዚህ በመንግስት ግልበጣ የተጠረጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው በመትረፉ አሁንም በዝዋይ ወህኒ ቤት ይገኛሉ።