ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2009)
ከወራት በፊት በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው እስረኞች ቁጥር 121 መድረሱ ተገለጸ።
የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ ከአንድ ወር በፊት በእስር ቤቱ ደርሶ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተያያዘ 38 እስረኞች ክስ እንደመሰረተባቸው ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ቁጥሩ ወደ 121 ከፍ ማለቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በይፋ ክስ የተመሰረተባቸው 121 ዱ ተከሳሾች ለ23 እስረኞች ሞት ምክንያት ሆነዋል እንዲሁም በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ንብረት በእሳት እንዲጋይ አድርገዋል የሚል የጋራ ክስ እንደተመሰረተባቸው መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
በቂሊንጦ እስር ቤት በነሃሴ ወር አጋማሽ ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ ከ20 የሚበልጡ እስረኞቹ ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ እማኞች እስረኞቹ በተኩስ ድርጊት መሞታቸውን ለኢሳት እና ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የእስር ቤቱ ሃላፊዎች በበኩላቸው ከ20 የሚበልጡ እስረኞች በመረጋገጥና በትንፋሽ ማጠር ምክንያት መሞታቸውን በመግለጽ የእማኞችን መረጃ አስተባብሏል።
በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎው አደጋ ደርሶ በነበረ ጊዜ ያለመሳሪያ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ የጸጥታ ባልደርባ የታጠቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በእስረኞች ላይ የተኩስ ዕርምጃ መክፋታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ለተሰኘ መጽሄድ አስረድቷል። ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ይኸው የጸጥታ አባል በርካታ እስረኞች የእሳት አደጋውን ለማጥፋት ርብርብ ሲያደርጉ ማየቱምን ገልጿል።
ይሁንና የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳዳሪዎች ህይወታቸው ካለፈ እስረኞች መካከል ሁለት ብቻ ለማምለጥ በሞከሩ ጊዜ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቋል።
ክሱን የመሰረተው ከሳሽ አቃቤ ህግ በበኩሉ ለወራት ያህል “ከእስር እናመልጣለን” የሚል ዕቅድ ነድፈው ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ያላቸው እስረኞች ተባባሪ ባልሆኑ እስረኞቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማድረጋቸውን በክሱ አስፍሯል።
ተከሳሾቹ በተናጠል፣ በጋራ፣ በቡድን በመሆን በማረሚያ ቤቱ ላይ በፈጸሙት የእሳት ቃጠሎና የሰው መግደል ወንጀል የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት ሊወድም መቻሉን አብራርተዋል።
ሁሉም ተከሳሾች በሌላ ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን፣ በመካከላቸው የስዊድን ዜግነትን ያላቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ይገኙበታል። የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ወር ዜጋው ከእሳት ቃጠሎው ጋር በተገኛኘ ተደራራቢ ክስ የተመሰረተባቸው ኣካሄድ አሳሳቢ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
በልብ ቀዶ ህክምና ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ዶ/ር ፍቅሩ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ከሶስት አመት በፊት ለእስር መዳረጋቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አውስቷል።