በቂሊንጦ እስር ቤት ከእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የቤተሰቦቻቸውን   ሁኔታ ለማወቅ የጠየቁ ቤተሰቦች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ታሰሩ

ጳጉ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :-የእስረኞች ቤተሰቦች ላለፉት አምስት ቀናት የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ወደ ቅሊንጦ እስር ቤት ተመላልሰዋል። በገዢው ፓርቲ በኩል 23 ሰዎች እንደሞቱ ከመገለጹ በስተቀር የሟቾቹን ቁጥር በዝርዝር ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። አብዛኞቹ ሟቾች በጥይት መሞታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቁጥሩ ገዢው ፓርቲ ከጠቀሰው በእጥፍ ከፍ እንደሚል መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያውያን በድርጊቱ በመበሳጨት ሃዘናቸውን እየገለጹ ባለበት ወቅት፣ በገዢው ፓርቲ በኩል የሟቾችን ዝርዝር ይፋ ለማድረግ አለመፈለጉ ሃዘኑና ብስጭቱ እንዲቀጥል አድርጎታል። በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ የሆኑት ቤተሰቦች ዛሬ ቂሊንጦ አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ፣ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ቢጠይቁም፣ የጠበቃቸው ግን የፖሊስ ዱላና እንግልት ነበር። አንዳንድ ቤተሰቦችም ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

እናቶችን ማጽናናት ሲገባ፣ እንዲህ አይነቱ እርምጃ መወሰዱ ፍጹም አረመኔነት ነው በማለት የገለጸች አንድ በስፍራው የነበረች የአንድ እስረኛ እህት፣ በወንድሟ እጣ ፋንታ አለመታወቅ ከተሰማት ሃዘን በላይ የፖሊሶች ድርጊት በእጅጉ እንደጎዳት ተናግራለች።

ዛሬ  አስከሬን ለቤተሰብ እንዲሰጥ ማድረግ የጀመሩት ፖሊሶች፣ አስከሬን ለቤተሰብ ካስረከቡ በሁዋላ፣ ሟቹ በምን እንደሞተ እንዳይታወቅ አስከሬን መክፈት እንደማይቻል ለቤተሰቦች ትእዛዝ ሰጥተዋል። ፖሊሶቹ አስከሬኑ እስኪቀበር ድረስ አብረው በመጓዝ ቁጥጥር ሲያደርጉ መዋላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለኢሳት ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት እነዚህ ቤተሰቦች  ፣ ፖሊሶች ልጃቸው በእሳት ተቃጥሎ እንደሞተ ቢነገራቸውም እንዳላመኑ ገልጸዋል። ልጃችን በጥይት ተመትቶ ባይገደል ኖሮ አስከሬኑን ከፍተን እንመልከተው ስልን አይከለክሉንም በማለት ገልጸዋል።