ኢሳት (ነሃሴ 30 ፥ 2008)
በቂሊንጦ እስር ቤት እሳት ከመነሳቱ በፊት እስረኞች መገደላቸውንና የእሳት ቃጠሎ የተፈጸመው ግድያውን ለመሸፈን ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ቅዳሜ ዕለት ንጋት ላይ ከ2:30 ጀምሮ ለሁለት ሰዓታት ያህል እስር ቤቱ በእሳት የጋየ ሲሆን፣ ከእሳቱ ሸሽተው ህይወታቸውን ለማዳን የሞከሩ ሰዎች ማማ ላይ በነበሩ ጠባቂዎች በተተኮሰ ጥይት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከእስር ቤት ሊያመልጡ ሲሉ ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ 4 እስረኞች ከተገደሉ በኋላ እስር ቤቱ በእሳት እንዲያያዝ ተደርጓል። ከዚያ ከቀጠሎ ለመሸሽ የሞከሩትን ማማ ላይ ሆነው ጥበቃ ላይ በነበሩ ፖሊሶች ጥይት ተርከፍክፎባቸዋል።
ከአሰቃቂው ጭፍጨፋ በኋላ እስር ቤቱ የተዘጋ ሲሆን፣ ከ60 የሚበልጡ ግድያ የተፈጸመባቸው እስረኞች አስከሬን በተለያዩ ሆስፒታሎች ከቤተሰብ ተደብቀው ተቀምጠዋል።
አስከሬኖቹ በጦር ሃይሎችና በአብዮት ሆስፒታል እንደሚገኙ ሲነገር፣ በሆስፒታል ውስጥ ባለው አስከሬን ማቆያ ማንነታቸው እንዳይታወቅ በኮድ መቀመጣቸውን የኢሳት የሆስፒታል ምንጮች ጠቁመዋል። ከእነዚህ አስከሬኖች ውስጥ በአብዮት ሆስፒታል የነበሩ በወታደር መኪና ወደ ሌላ ቦታ መወሰዳቸውን አስረድተዋል።
ሃኪሞች አንድም ሰው በእሳት ተቃጥሎ እንዳልሞተ ያረጋገጡ ሲሆ፣ በሆስፒታሎች የሚገኙት አስከሬኖች በጥይት የተበሳሱ እንደሆነም ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ በአብዮት ሆስፒታል ከ26 በላይ አስከሬኖች ተቆልፎባቸው ከቤተሰቦቻቸው ተደብቀው ይገኛሉ።
ከ3 ሺ በላይ እስረኞች ቤተሰቦች “ቂሊንጦ ተዘግቷል ሌላ ቦታ ፈልጉ” በመባላቸው በማዕከላዊ፣ በዝዋይ፣ በሸዋሮቢት፣ በቃሊቲ እና ሌሎች እስር ቤቶች ፍለጋ ቢያደርጉም ጥሩ ዜና መስማት አልቻሉ። የኦፌኮ አመራር ደጀኔ ጣፋ ባለቤት ወይዘሮ አሰለፈች ሙላቱ የ3 ቀን ጥረታቸው ተስፋቸውን እንዳጨለመና በየሆስፒታሉ ያለው ጥበቃ ስጋታቸውን እንደጨመረ ገልጸዋል።
የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር እሁድ ዕለት በ3 ቀናት ውስጥ አሳውቃለሁ ቢልም ዛሬ ከ5 ቀናት በኋላ ዝርዝራቸው እንደሚያሳውቅ ገልጿል።