ኢሳት (መስከረም 3 ፥ 2009)
በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእስት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ ከአደጋው የተረፉ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደ ስፍራው ያቀኑ ጠያቂዎች በእስር ቤቱ አስተዳደር እገዳ መጣሉን ለኢሳት አስታውቁ።
የእስረኛ ቤተሰቦች የቤተሰብ አባሎቻቸውን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤቱ ቢሄዱም የያዙትን ነገር ብቻ አቀብለው ያለምንም ንግግር እንዲመለሱ መደረጉን ከዜና ክፍላችን ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉ ቤተሰቦች ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በቂሊንጦ እስር ቤት ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሶስት ዞኖች ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ አንደኛው ዞን ከቃጠሉ መትረፉ ታውቋል።
ይሁንና ከዚህ ቃጠሎ የተረፉ እስረኞችን ለመጠየቅ ቤተሰቦች ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቤተሰቦች እገዳ እንደተጣለባቸው ለደህንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የቤተሰብ አባላት ለኢሳት አስረድተዋል።
ከአደጋው በተረፉ እስረኞች ላይ ድንጋጤና አለመረጋጋት እንደሚታይ የተናገሩት ቤተሰቦች የቤተሰብ አባሎቻቸውን በአይን ብቻ አይተው እንደሚመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
በቂሊንጦ እስር ቤት ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ለዜና ክፍላችን ያስረዱት የእስረኛ ቤተሰቦቹ የእስረኞቹን ችግርና ያሉበትን ሁኔተ በአግባቡ መረዳት ሳይችሉ መቅረታቸውን አክለው አስታውቀዋል።
በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ በእስር ቤቱ የተኩስ ድምፅ መሰማቱንና ከ20 በላይ እስረኞች መገደላቸውን እማኞች ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በእለቱ በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ አንድ የጸጥታ አባል የታጠቁ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እስረኞችን ኢላማ ያደረገ የተኩስ እርምጃ ሲወስድ መመልከቱን በሃገር ቤት በሚታተም መጽሄት (አዲስ ስታንዳርድ) አስረድቷል።
መንግስት የእስረኞቹን መሞትን ቢያረጋግጥም፣የሟቾችን ማንነት ግን እስካሁን ድረስ ይፋ ሳያደርግ ቆይቷል።
የኢሳትን ቃጠሎ አደጋን ተከትሎ ከ2ሺ በላይ እስረኞች በተለያዩ የፌዴራልና የክልል እስር ቤቶች እንዲዛወሩ የተደረገ ሲሆን፣ በእስር ቤቱ የደረሰው የእሳት አደጋ በምን ምክንያት እንደደረሰ የታወቀ ነገር የለም።