ኢሳት (ጥር 8፥ 2009)
በቂሊንጦ እስር ቤት ለሚገኙ ታሳሪዎች ገንዘብና የሞባይል ስልክ ለማስገባት ተባብረዋል የተባሉ አምስት የእስር ቤቱ የጥበቃ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመሰረተባቸው።
የአምስት የጸጥታ አባላት መጠኑ ከ316ሺ ብር በላይ የሆነ የገንዘብ እንዲሁም የእጅ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ከውጭ ወደ እስር ቤቱ እንዲገባ በማድረግ እንዲሁም ከታራሚዎች የሚላኩ መልዕክቶችን ለጋዜጠኞች እንዲደርስ አድርገዋል የሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ስማቸው የተገለጸው እነዚሁ አምስት የቂሊንጦ እስር ቤት ፖሊሶች በሽብርና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከተከሰሱ እስረኞች ጋር በመስማማት ድርጊቱ ከታህሳስ 2008 ዓም እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2008 አም ድረስ መፈጸማቸውን ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።
ይሁንና ገንዘቡን እና የእጅ ስልኩን ተቀብለዋል የተባሉት እስረኞች ማንነት ያልተገለጸ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በሌሉበት ክሱ መመስረቱን ለመረዳት ተችሏል።
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተጠርጣሪዎቹን ሲያቀርብ ክሱ የሚነበብላቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ይሁንና ተጠርጣሪ ፖሊሶቹ ለችሎት ያልቀረቡበት ሁኔታ አልተገለጸም።
መሳይ በላይ፣ ጌታቸው ሰይድ፣ ዋና ሳጅን ሃጎስ ወልደስላሴ፣ ፍላቴ ትላም፣ እና ምክትል ኢንስፔክተር ገመቹ ዳንዳ ኢታኮ አምስቱ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላት መሆናቸው ተመልክቷል። በነሃሴ ወር 2008 አም በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ ከ100 የሚበልጡ እስረኞች የእሳት ቃጠሎን በማድረስና ከውጭ ካሉ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ግንኙነት አድርገዋል ተብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።
ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በአደጋው ለሞቱ ወደ 22 ሰዎች አካባቢ ተጠያቂ ናቸው ሲል በክሱ አስፍሯል።
አደጋው በደረሰ ጊዜ እማኝነትን የሰጡ ነዋሪዎችና አንድ የእስር ቤቱ የጸጥታ ባልደርባ በወቅቱ የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ ዕርምጃ መውሰዱን እና እስረኞቹ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።