ታኀሳስ ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን ወደ የመን ሲጓዝ የነበረ ጀልባ ሰጥሞ ከ79 ያላነሱ ኢትዮጵያዊያን ያለቁ ሲሆን እስካሁን ከ14 ያልበለጡ ሰዎች ብቻ አስከሬን መገኘቱን ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሃይማኖት ገልጿል። የሟቾች ቁጥር አስቀድሞ በመገናኛ ብዙሃን እንደተገለጸው ሳይሆን 79 መሆኑን ግሩም አክሎ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕጋዊ ጉዞን ከአንድ ዓመት በላይ አግዶ በመቆየቱ በየጊዜው ለሚሞቱ ሰዎች ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በሚሄዱ ኢትዮጵያዊን ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባስ አሳስቦኛል በሚል በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም የተደረገው የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት፣ ሕገወጥ ሥራው ይበልጥ እንዲጠናከር መንገድ መክፈቱን ያስታወሱት ምንጮቹ በዚህ ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰው እንግልትና መከራ በአሳዛኝ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ።
ሰሞኑን ወደየመን ሲጓዙ ያለቁት ወገኖችም ለዚህ ችግር የተዳረጉት ሕጋዊ መንገዱ ስለተዘጋባቸው መሆኑን አስታውሰው ለዚህ ክስተት ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ሃላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተያዘዘ ዜና ወደ አረብ ሀገራት ለስራ በሚሄዱ ዜጎችን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቀነስ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል የተረቀቀውና በዚህ ዓመት በፓርላማ ጸድቆ ወደስራ ይገባበታል የተባለው፣ አሁን በስራ ላይ ያለውን የግል ሥራና ሠራተኛን የማገናኘት አዋጅ ቁጥር 632/2001 የሚያሻሽለው ረቂቅ አዋጅ ገና በረቂቅነቱ ውዝግብ ገጥሞታል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከስምንተኛ ክፍል በታች ያሉ ዜጎች ወደአረብ ሀገራት መሄድ እንደማይችሉ መደንገጉ ሕገወጥ መንገዱን ለማጠናከር የሚረዳ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 632/2001 መሰረት ከ 400 በላይ ሥራና ሠራተኛን አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቋቁመው ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን የቤት ሠራተኞችን ወደተለያዩ የአረብ ሀገራት ሲያስቀጥሩ የቆዩ ቢሆንም በአለማቀፍ ጫና ምክንያት መንግስት ጉዞውን በማገድ ሕጉን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው በማለት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የጉዞ እገዳው ከተጣለ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን አብዛኛዎቹ ኤጀንሲዎች ሥራው ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ ለቤት ኪራይና ለሠራተኞች ደመወዝና ለሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎች በመዳረጋቸው ሥራውን ለመተው፣ አንዳንዶቹም ለመቀየር መገደዳቸው ታውቋል፡፡ በዚሁ የአዋጅ ማሻሻያ መሰረት በመንግስት ደረጃ ስምምነት ወደሌለባቸው ሀገራት ሠራተኞችን መላክ የሚከለከል ሲሆን የሚላኩ ሠራተኞችም ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቁ ሊሆኑ እንደሚገባ ደንግጎአል፡፡ አንዳንድ ሠራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች ይህ ረቂቅ አዋጅ በተለይ በትምህርት ላይ ገደብ ማበጀቱ ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ያደርጋል በማለት አንቀጹ እንዲነሳ ከወዲሁ እያሳሰቡ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በእገዳ ላይ የቆየው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መቼ ተነስቶ ሥራው እንደሚጀመር አሁንም የታወቀ ነገር እንደሌለ የጠቆሙት ምንጮቻችን በዚህ ምክንያት ሕገወጥ ጉዞው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡