ሐምሌ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቁጥራቸው ከስምንት ሽህ በላይ የሚሆኑ ቤተ እስራኤላዊያን እስራኤል ውስጥ ከሚገኙት ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት እየተጠባበቁ ሲሆን አብዛሃኞቹ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ከወላጆቻቸው የተለያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ”እነዚህ አይሁዳዊያን ናቸው በየዕለቱም ይፀልያሉ” ሲሉ ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴሩ በበኩላቸው ”ውሳኔ በአፍጣኝ ያልተሰጣቸው በዘረኝነት ተፅዕኖ ምክንያት ነው”ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።የአገሪቱ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽንና የአገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚቴ ጉዳዩን በጋራ አይቶ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ገልፀዋል።የመንግስት ተወካዮች የስደተኞቹ ቤተሰቦች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች፣በኅብረት ሆነው ውይይታቸውን ቀጥለዋል ሲል ያ ኔት ኒውስ ዘግቧል።
በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያን የሚፈጸምባቸውን አድልዎ በመቃወም በቅርቡ ተከታታይ ተቃውሞ አድርገዋል።