በሽንሌ ዞን ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ/ም) በሶማሊ ክልል በሽንሌ ዞን የተጀመረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። ባርባርታ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ወጣቶች የአብዲ አሊን አገዛዝ በመቃወም የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን በመጠየቅ ላይ ሲሆኑ ፣ ሃድሃጋላ በሚባለው አካባቢ የክልሉ ልዩ ሃይል በነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈቱ ታውቋል።
በተኩስ ልውውጡ ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ የታወቀ ነገር የለም። ትምህርት ቤቶችና መንግስታዊ አገልግሎት ተቋማት ሁሉ ተዘግተዋል። ወታደሮች በየቦታው ቁጥጥር እያደረጉ ቢሆንም፣ የህዝቡን ተቃውሞ ለማስቆም አልቻሉም። ላለፉት 2 ቀናት በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የታሰሩ ሲሆን፣ ህዝቡም ወጣቶች በታሰሩ ቁጥር ቁጣውን እየገለጸ ተቃውሞውን እያጠናከረ ነው።
ተቃውሞው ወደ ሌሎች የኢትዮ-ሶማሊ አካባቢዎች ሊሰራጭ ይችላል በሚል ፍርሃት አብዲ አሌ በተለይ በጅግጅጋ የልዩ ሃይል አባላቱን በብዛት አሰማርቷል።
የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ሻለቃ አሊ ስምሬ ሲገድ በሽንሌ የሚካሄደው ተቃውሞ አብዲ ኢሌን ከክልን አመራር እንዲወርድ ጭምር የሚጠይቅ ነው። አብ ኢሌ ወደ ድሬዳዋ ሽንሌና ሌሎችም አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ልኮ በማከፋፈል ለማረጋጋት ቢሞክርም አልተሳካለትም ሲሉ ሻለቃ አሊ ተናግረዋል።
ተቃውሞው ወደ ደገሃቡር መስፋፋቱንም ሻለቃ አሊ ተናግረዋል።
በሶህዴፓ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ክልሉን ወደ እርስ በርስ ግጭት ይመራዋል ተብሎም ተፈርቷል። አብዲ ኢሌ የፓርቲውን ሊቀመንበርና ክልሉን አፈ ጉባኤ ሞሃመድ ራሽድ ኢሳቅን በማባረር ራሱን የፓርቲው ዋና ሊቀመንበር አድርጎ መሾሙ ውዝግብ ፈጥሯል።