መጋቢት ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ የተከሰሱ የቀድሞው የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እንዲሁም የአረና ፓርቲ አመራር መምህር አብራሃ ደስታ ከሌሎች 6 ተከሳሾች ጋር መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓም ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀዋል።
ችሎቱን የተከታተለው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስ ቡክ አካውንቱ ባቀረበው ዘገባ ተከሳሾች አንድ በአንድ በክሱ ላይ የቀረበውን ወንጀል መፈጸማቸውንና አለመፈጸማቸውን በዳኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። አንደኛው ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ “አቃቢ ህግ ባላደረኩት ነገር ስለሆነ የከሰሰኝ መከራከሩ ህጉን መደገፍ እንዳይሆንብኝ መልስ አልሰጥም” ብሎአል። ዳኛው ክሱን ክደው ተከራክረዋል በሚል አስፍረዋል።
አቶ ሃብታሙ አያሌው ደግሞ ሽብር አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል፣ እረዳለሁም፣ አቃቢ ህግ ለምን እንደከሰሰኝም አውቃለሁ፣ የቆምኩለትን ህጋዊ ፓርቲንም አፍርሶታል።’ ሲል መልስ ሰጥቷል።
ሶስተኛው ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ በበኩሉ ሽብር የሚባለውን ቃል የሰማው ከኦሳማ ቢንላደንና ከአቶ መለስ ዜናዊ መሆኑን ገልጾ፣ ፈጽመህዋል የተባልኩት ነገር ሃይማኖቴም ዓላማዬም አይፈቅድም ብሎአል፡፡ ቤቴ እንዲወሰድበት መደረጉን የገለጸው አቶ ዳንኤል ፣” እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ሽብር ለመፈጸም ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ መንግሥት ፓርቲዬን ለማፍረስ የፈነቀለው …›› ብሎ በመናገር ላይ እንዳለ ፍርድ ቤቱ ንግግሩን እንዲያቋርጥ እንዳስገደደው ኤልያስ ዘግቧል።
በአራተኛ ደረጀ የተከሰሰው አብርሃ ደስታ ደግሞ ገና መናገር ሲጀምር ‹‹ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸምህን ብቻ ተናገር›› ተብሎ ከችሎቱ ማስጠንቀቂያ ተሰትቶታል። አብራሃ “የፈለኩትን እናገራለሁ፡፡ ሀሳቤን ልግለጽ›› በማለት መናገሩን፣ ዳኞችም ሳይዋጥላቸው እንዲናገር ፈቃድ እንደሰጡት በዘገባው ተመልክቷል፡፡
አብርሃ ‹‹ክሴ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት …የሚል ነው፡፡ አሸባሪ ማለት ለሚፈልገው ዓላማ ፣ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ሰውን የሚጎዳ ድርጊት የሚያስፈጽም ማለት ነው፡፡ ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ …›› ብሎ ሲናገር የግራ ዳኛው የአብርሃን ንግግር አቋርጠው ‹‹ክሱ ላይ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚል የለም፡፡ ክሱን መቃወም አለመቃወምህን ብቻ ተናገር›› ብለውታል። አብርሃምም ‹‹ሕወሃት /ኢህአዴግ፣ ደህንነቱ ማፊያ ነው … ›› ብሎ እንደገና መናገር ሲጀምር ዳኞቹ አቋረጡት።
የሺዋስ አሰፋ ደግሞ ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምናገረው፣ ስሙኝ በማለት አቤቱታ ቢያቀርብም ዳኞቹ ክሱን መቃወም አለመቃወሙን ብቻ እንዲናገር አዘውታል፡፡ የሺዋስ እድሉን ተጠቅሞ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 75/4 ላይ ልዩ ፍርድ ቤት ስለማቋቋም ይደነግጋል፡፡ ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ዳኞች ነጻ ስለመሆናቸው ይደነግጋል፡፡ የእኔ ችግር ችሎቱ ላይ ነው፡፡›› ሲል ዳኞች የየሺዋስን ንግግር አቋርጠውታል፡፡ የሺዋስም ቀጥሎ ‹‹በሕገ-መንግሥቱ ላይ ዳኞች ነጻ መሆን እንዳለባቸው ቢቀመጥም የመርማሪ እና ዐቃቤ ሕጎችን ሀሳብ ብቻ ይሰማል፤ እኛን አይሰማንም፣ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ነው፡፡…›› ሲል ዳኞች አስቁመውታል።
በ6ኛ ደረጃ የተከሰሰው ዮናታን ደግሞ ‹‹ያለፈቃዳችን እንድታናግሩን እየተገደድን ነው›› ብሏል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ‹‹የተቀነባበረ ክስ ስለሆነ ምንም ማለት እንደማይችል ሲገልጽ፣ 8ኛ ተከሻሽ ባህሩ ታዬም ‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ውስጥ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም፣ አለፈጸምኩምም፡፡ ጊዜ እውነቱን ይፈርዳል›› ብሎአል። 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል።
ችሎቱ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 13፣ 14 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ተነስቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በእነ ሶሊያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በሽብር ወንጀል የተከሰሱት የ ዞን 9 ጦማሪያና ጋዜጠኞች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቢቀርቡም የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
አቃቤ ሕግ ያቀረበው የኦዲዮ ሲዲ ማስረጃ እንዲደርሳቸው ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ችሎቱ ብይኑን ስላልጨረሰ ለመጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡