ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንደኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በሌለችበት፣ሶስተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ ፣ አምስተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ፣ስድስተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ የተሰናበቱ ሲሆን፣ ሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ከሽብር ክስ ነፃ የተባለ ቢሆንም ማአከላዊ ምርመራ በኃይል እና በማሰቃየት የሰጠው ቃል ላይ አመፅ እንዳነሳሳ አምኗል በሚል በወንጀል ህጉ 257 መሰረት እንዲከላከል ይሁን እንጅ ዋስትና መጠየቅ እንደሚችል ፍርድቤቱ ወስኗል።
የጦማርያኑ ጠበቃ በፍቃዱ ይግባኝ እንዲሰጠው የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ሕግ ተቃውሞ አሰምቶ ይግባኙ ላይ ለመወሰን ለጥቅምት 10 ለማየት ቀጠሮ ሰጥቷል። በነጻ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ጸሃፊዎች የመፍቻ ወረቀት አልደረሰንም በሚል እስር ቤቱ ሳይፈታቸው በመቅረቱ ቅዳሜና እሁድን በእስር ቤት ሊያስልፉ ይችላሉ። ምንም እንኳ ጸሃፊዎቹ በነጻ የተለቀቁ ቢሆንም አሁንም እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጋዜጠኞችም በእስር እየተንገላቱ ነው።