(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 16/2010)
በአሸባሪነት ተወንጅሎ እድሜ ልክ የተፈረደበትንና የካናዳ ዜግነት ያለውን ኢትዮጵያዊ በሽር ማክታልን ከእስር ለማስለቀቅ ዘመቻ ተጀመረ።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር አባል ነው በሚል ከኬንያ በሃይል ተገዶ ወደ ኢትዮጵያ የተወሰደውና በአሸባሪነት የተወነጀለው በሽር ማክታል ከታሰረ 11 አመታት ተቆጥረዋል።
የ49 አመት እድሜ ያለው በሽር ከእስር እንዲለቀቅ ካናዳውያን ዘመዶቹና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ዘመቻ ጀምረዋል።
የካናዳ ዜግነት ያለው በሽር ማክታል ለንግድ ስራ ወደ ሶማሊያ ማምራቱን ቤተሰቦቹና በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።በጎረቤት ሶማሌያ በንግድ ስራ ላይ ይተዳደር የነበረው በሽር ግን የኢትዮጵያ ወታደሮች አልሻባብን ለመዋጋት በአካባቢው ዘመቻ ሲያካሂዱ በነበረው ውጊያ ወደ ኬንያ ድንበር መሸሹ ነው የሚነገረው።
በዚህ አጋጣሚ ለኬንያ ባለስልጣናት እጁን የሰጠው በሽር አለም አቀፍ ህግን ባልጠበቀ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱ አሁን ላለበት የእስርና እና የሰቆቃ እንግልት ተዳርጓል ተብሏል።የካናዳ ዜግነት ያላት ባለቤቱ አሲሶ አብዱ እንደምትለው በሽር ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰረው በሕገወጥ መንገድ ነው።
በግል አውሮፕላን ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ተገዶ ከተወሰደ በኋላም በሽብር ወንጀል ተከሶ እድሜ ልክ እንደተፈረደበትም መገለጹ ይታወሳል።የበሽር አያት የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የአመራር አባል ከመሆናቸው ውጪ በሽር በሶማሌያ የንግድ ስራ ብቻ ይሰራ እንደነበር ቢነገርም በሐሰት ተወንጅሎ ሰቆቃ እንደተፈጸመበትም ተነግሯል።
እናም በአሁኑ ጊዜ እስረኞች በምህረትና ይቅርታ ሲለቀቁ በሽር ሊዘነጋ እንደማይገባ በመግለጽ ካናዳውያን ዘመዶቹና አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ዘመቻ ጀምረዋል።
ባለቤቱን ጨምሮ የካናዳ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዲዮ በኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎችም የበኩላቸውን ግፊት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል።
የካናዳ ፓርላማ ጸሃፊና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠሪ ባለቤቱን በኢትዮጵያ አግኘተው በማነጋገር በኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ በሽርን ለማስፈታት ጫና እያደረጉ መሆናቸው ነው የተነገረው።የኢትዮጵያው አገዛዝ ግን ኦብነግ በሽብርተኝነት የተፈረጀና በሽርም የዚሁ ድርጅት አባል ስለሆነ ዜግነቱ ካናዳዊ ቢሆንም ከእስር አይለቀቅም ማለቱን አልጀዚራ ዘግቧል።