በሻኪሶ ተቃውሞ አገረሸ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 29/2010) በሻኪሶ ዳግም ተቃውሞ አገረሸ።

የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ ለተጨማሪ አስር ዓመት ኮንትራቱ መራዘሙን ተከትሎ ከአንድ ሳምንት በፊት የጀመረው ተቃውሞ ቀጥሏል።

ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ የሻኪሶ ከተማ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙ ታውቋል።

ለገንደንቢ የሜድሮክ ወርቅ ማምረቻ ጠቅላላ ስራ ማቆሙንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከሻኪሶ ወደ አዶላና እና ወደተለያዩ ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ተዘግተዋል።

የኢሳት ወኪል ካደረሰን መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው የግልም ሆኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በሙሉ ዝግ ናቸው።

በሌላ በኩል በሞያሌ አዲስ ግጭት መቀስቀሱን ዘግይቶ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የቀድሞው የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የአሁኑ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ቅዳሜ ሻኪሶ ነበሩ።

በህዝቡ ተቃውሞ የቀረበበትን የሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ የ10 ዓመት ኮንትራት በቀጥታ እጃቸውን ያስገቡት እኚህ ባለስልጣን የአካባቢውን ነዋሪ ለመጎብኘትና ለማነጋገር ሰሞኑን እዚያው ሻኪሶ ቆይተዋል።

ቅዳሜ ዕለት የሜድሮክ የወርቅ ማዕድን በሚጠቀመው ኬሚካል የተጎዱ በርካታ ነዋሪዎችን ሰብስበው አነጋግረው እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ትላንት ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎችን ጨምሮ ከሻኪሶና ክብረመንግስት ነዋሪዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው ነበር።

አቶ ሞቱማ የተፈጸመውን ጉዳት ዕውቅና ቢሰጡትም ኮንትራቱ እንደሚሰረዝ ግን ዋስትና መስጠት የሚችሉ ሰው ሆነው አልቀረቡም።

ነዋሪው የደረሰበትን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለባለስልጣኑ ቢያሳውቁም መፍትሄ ሊያገኝ የሚችልበት ስብሰባ አልሆነም።

ሳይጠናቀቅ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

የትላንቱን ያለስምምነት የተጠናቀቀ ስብሰባ ተከትሎ በዛሬው ዕለት የሁለቱ ከተሞች ነዋሪ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል።

የሻኪሶና የአዶላ – ክብረመንግስት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ተዘግተው በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ለሜድሮክ የወርቅ ኩባንያ የተሰጠው ተጨማሪ 10 ዓመት ኮንትራት በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ተጠይቋል።

ስብሰባው ከተጨናገፈበት ሰዓት ጀምሮ ከሁለቱ ከተሞች ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እንዳልተከፈቱ ታውቋል።

ሻኪሶ ከቀትር በኋላ የተቃውሞው ሰልፍ ቢቆምም በከተመዋ የሚደረገው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ግን ቆሞ እንደዋለ ለማወቅ ተችሏል።

ከአዶላ ነጌሌ በረና የሚወስድው ዋናው መስመርም ተዘግቶ እንደነበረ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሜድሮክ የለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ድርጅት ሰራተኞች በተፈጠረው ተቃውሞ የተነሳ ዛሬ ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው መዋላቸው ተገልጿል።

የአከባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ ሳያደርግ ለተለያዩ ለህይወት አስጊ በሆኑ በሽታዎች እንዲጠቃ ያደረገው የለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ድርጅት ለተጨማሪ 10 ዓመታት ኮንትራቱ እንዲራዘም መደረጉ ያስነሳው ቁጣ እንደቀጠለ ሲሆን የህወሀት አገዛዝ ኮንትራቱ እንደማይሰረዝ አስታውቋል።