በሸዋሮቢት ከተማ ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ ደረሰ

ሚያዚያ ፲፪(አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋሮቢት ከተማና አካባቢው ባሉ አጎራባች ቀበሌዎች ላይ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቀሉ። ጎርፉ መጠነሰፊ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳትቶችን አስከትሏል።
እስካሁን የደረሰውን የንብረት ውድመት በውል ለይቶ አሃዙን ማስቀመጥ ባይቻልም በሸዋሮቢት ከተማ ብቻ ባሉ አራት ቀበሌዎች ውስጥ ከአራት መቶ በላይ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ አደጋ ወድመዋል። ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ቤት ንብረታቸውን ከማጣታቸው በተጨማሪ በከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ጎርፉ ተፈጥሯዊ አደጋ ቢሆንም በተለይ የሸዋ ሮቢት ከተማን መሃል ለመሃል አቆራርጦ የሚያልፈው ወንዝ አቅጣጫውን እንዲቀይር የከተማው ነዋሪዎች ተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ሰሚ አላገኙም።
የፍሳሽ መውረጃ ትቦዎች መደፈን፣ ተለዋጭ አለመሰራት፣ በነባሮቹም ላይ እድሳት አለመደረጉ እንዲሁም ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ የከተማ ልማት አለመዘርጋቱ የችግሮቹ ምንጮች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የመጓጓዣ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል። ግብረሰናይ ድርጅቶች ለተጠቂ ቤተሰቦች እርዳታ እያቀረቡ ሲሆን እስካሁን ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ምን ያህል አደጋ እንደደረሰ በግልጽ ማወቅ አልተቻለም።። በቅርቡ በጅጅጋና መርሳ ከተሞች ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ማድረሱ ይታወሳል።