በሶማሌ ክልል የከፋ የምግብ እጥረት ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የምግብ እርዳታ ለማግኘት በ24 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተሰባስበው በሚገኙ ሰዎች መካከል እየደረሰ ያለው የከፋ የምግብ እጥረትና ጉዳት በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው አህዝ በሶስት እጅ መብለጡ ስጋት እንዳሳደረበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።

በክልሉ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ከ20ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲሰባሰቡ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና እርዳታ ፈላጊዎቹ በቂ የምግብ አቅርቦት እየደረሰባቸው ባለመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የ15 በመቶ የጉዳት መጠን በሶስት እጅ እጥፍ መጨመሩን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።

የከፋ የምግብ እጥረት እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ ከ24ቱ መጠለያዎች መካከል በዘጠኙ ተከስቶ የሚገኘው የደም ማነስ የጤና ችግር ከ40 በመቶ በላይ ማሻቀቡንና ቁጥሩ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን መጠን እንዳለፈ ታውቋል።

በሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ መጠለያ ጣቢያ እንዲሰባሰቡ ከተደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት የከፋ የምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውንም ተመድ ገልጿል።

ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ተመሳሳይ ሪፖርት በተለይ በሶማሌ ክልል እየተባባሰ ያለው የድርቅ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አደጋ ውስጥ እንደከተተ ማስታወቁ ይታወሳል። አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው በክልሉ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በማሳሰብ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎረቤት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እንዲሁም በኬንያና ዩጋንዳ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከ21 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ እርዳታ እንዲጋለጡ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በጎረቤት ደቡብ ሱዳን ይኸው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ የተለወጠ ሲሆን፣ ችግሩ በሌሎች ሃገራትም ሊዛመትም ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ የኦሮሚያ አፋር፣ ሶማሌና የደቡብ ክልሎች በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደሚገኙ ይታወቃል።