(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 4/2010) በሶማሌ ክልል ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች በህወሃት መሪዎች ተገደን የፈጸምነው ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ አብዲ ዒሌ ይህን የተናገሩት ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።
አብዲ ኢሌ የቀድሞ የደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋን በስም በመጥቀስ እያስገደዱን ወንጀል እንድንፈጽም ያደረጉን ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድንና አቶ ለማ መገርሳን በማወደስ ለኢትዮጵያ መልካም ነገር የሚያደርጉ ናቸው በማለት የገለጹት አብዲ ዒሌ የይቅርታ ጊዜ በመሆኑ ያለፈውን እንርሳ ሲሉ ተማጽነዋል።
በሶማሌ ክልል በተፈጸሙ ወንጀሎች ከእሳቸው ጋር የሚነሱትን የህወሃት ጄነራሎችን አለመጥቀሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
አብዲ ዒሌ በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባው አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ጠንከር ያሉ ውንጀላዎችን አሰምተዋል።
እስከአሁን የተፈጸሙት ወንጀሎች ሁሉ በህወሀት መሪዎች በተለይም በቀድሞ ድህንነት ሃላፊ በነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ትዕዛዝና አስገዳጅነት የፈጸምናቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ ላይ አቶ አብዲ ዒሌ የህወሀት መሪዎችን በሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ለተፈጸሙ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ተጠያቂዎች ናቸው ማለታቸው ተጠቅሷል።
አቶ ጌታቸው አሰፋ ግንባራችን ላይ ሽጉጥ እየደቀኑ ጭምር ወንጀል እንድንፈጽም ያስገድዱን ነበር ማለታቸውን የምክር ቤቱን ውሎ የተከታተለው የሶማሌ ክልል ተወላጅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሙስጠፋ ኡመር ለኢሳት ገልጿል።
አቶ አብዲ ዒሌ ስለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝም አንስተው ለስድስት ዓመታት በነበራቸው ቆይታ አላሰራ በማለት ሲያስጨንቋቸው የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የህወሀትንና የአቶ ጌታቸው አሰፋን ስም በተደጋጋሚ እየጠቀሱም ‘’እኛ በእነሱ አስገዳጅነት የፈጽምናቸው ወንጀሎች እንጂ በራሳችን ያደረግነው ጥፋት የለም ማለታቸው ተገልጿል።
የቀድሞው ደህንነት ሃላፊ ገንዘብ እንድሰጠው ያስገድደኝም ነበርም ብለዋል።
ሰሞኑን ስልጣን እንደምለቅ ተደርጎ የተናፈሰው ወሬ ሆን ተብሎ በአቶ ጌታቸው አሰፋ የተሰራጨ ነው በማለት የከሰሱት አቶ አብዲ ዒሌ እኔን ከስልጣን ለማወረድ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም ሲሉ ገልጸዋል።
የአሁኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለኢትዮጵያ ከእግዚያብሄር የተላኩ መሪ ሲሉ አወድሰዋል።
አቶ ለማ መገርሳንም እንዲሁ ጥሩ ሰው ናቸው ማለታቸው ተጠቅሷል።
አቶ አብዲ ዒሌ ከአምስት ዓመት በፊት በድብቅ በተቀረጸ ቪዲዮ ላይ እንደተናገሩት የሶማሌ ወዳጅ ህወሀት ወይም ትግሬዎቹ ብቻ ናቸው።
ኦሮሞና አማራ ለእኛ ጠላት ናቸው ማለታቸው መጋለጡ የሚታወስ ነው። ባለፉት 10 ዕማታት በስልጣን በቆዩባቸው ጊዜያት በዋናነት ከህወሀት ጄነራሎች ጋር እጅና ጓንት በመሆን በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ወንጀሎችን መፈጸማቸው በማስረጃ ጭምር የተጋለጡት አቶ አብዲ ዒሌ በዛሬው ስብሰባ የጀነራሎቹን ስም አለማንሳታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ በግል ባላቸው ቂም የተፈጸሙትን ወንጀሎች በእሳቸው ላይ ማላከካቸው ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ ነገም ይቀጥላል ተብሏል።