ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል ጋሻሞ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘገቡ።
ግድያው የተፈጸመባቸው 42ቱ ሰዎች አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የዩኒስ ኢሳቅ ንዑስ ጎሳ አባላት መሆናቸውንም ሳላን ሚዲያ የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም አስነብቧል።
ግድያ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ ሁለት ንዑስ ጎሳዎች በጎረቤት ሶማሊላንድ አብዛኛውን ክፍል የሚይዙ መሆኑንና ድርጊቱ በአካባቢው ውጥረት ማንገሱን የዜና አውታሩ በዘገባው አስፍሯል።
ግድያ ከተፈጸመባቸው ሰዎች መካከል አብዲ ፋራ የተባሉ ታዋቂ ነጋዴ እንደሚገኙበትና ሁለት ወንድ ልጆቻቸውም በጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተገልጿል።
ለማክሰኞ ጥቃት ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም ከዚህ በፊት በአካባቢው በሚካሄዱ ግጭቶች በሶማሊ ክልል የሚገኘው ልዩ ሃይል ከጎሳ አባላቱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አለመባባት ውስጥ መቆየቱን የዜና አውታሩ አመልክቷል።
ራሷን እንደ ነጻ አገር አድርጋ ያወጀችው ሶማሊላንድም ሆነች የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ በቅርቡ የሶማላንድ ተወካዮች በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ በጸጥታ እና ደህንነት ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት ከጎሳ ጋር የተገናኙ ግጭቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውንና በርካታ ነዋሪዎች መሞታቸውን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ መቆየታቸውንም ታውቋል።