ኢሳት (ሚያዚያ 9 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በየዕለቱ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች ለህመም በመዳረግ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት እና የእርዳታ ድርጅቶች በበሽታው ወረርሽኝ ሰዎች በመሞት ላይ መሆኑን ቢያረጋግጡም መንግስት የሟቾች ቁጥርን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ይሁንና የበሽታ ወረርሽኙ በመባባስ ላይ መሆኑን ተከትሎ በወረርሽኙ በተጠቁ በርካታ ወረዳዎች በየዕለቱ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በበሽታው እየተያዙ መሆኑ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየዕለቱ 750 ሰዎች በበሽታው ሲያዙ መቆየታቸውን አረጋግጦ እየተካሄደ ባለው የበሽታውን ስርጭት የመቆጣጠር ዘመቻ ቁጥሩ 259 ላይ መገኘቱን ይፋ አድርጓል።
ከአማራ፣ ትግራይ፣ ሃረሪ ክልሎች እንዲሁም ከሃረማያና ጅጅጋ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ከ500 በላይ የጤና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት በክልሉ ተሰማርተው የኮሌራ በሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።
መቀመጫውን በቤልጂየም መዲና ብራሰልስ ከተማ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ባለፈው ሳምንት በዚሁ የበሽታ ወረርሽኝ ከ40 በላይ ሰዎች እንዲሞቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የበሽታ ስርጭቱ ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ቢያረጋግጥም እስከ አሁን ድረስ ምን ያህል ሰው እንደሞተ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።
በሃገሪቱ በሚገኙ አራት ክልሎች ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ የሶማሌ ክልል ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆን መጀመሩን የዕርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑት በሶማሌ ክልል ያሉ ነዋሪዎች መሆናቸው ተመልክቷል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁን ለመከላከል ላቀረበው የእርዳታ ድጋፍ በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት ችግሩ እየተባባሰና ወደ ከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሌራ በሽታ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሃገር አቀፍ ዘመቻው ተጠናከሮ መቀጠሉን ቢገልጽም የክልሉ ነዋሪዎች ስርጭቱ ወደ አዳዲስ ወረዳዎች ጭምር በመዛመት ላይ መሆኑን አስታቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በበኩሉ በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በመቶ ሺ በሚቆጠሩ ህጻናት ላይ የከፋ ጉዳትን እያስከተለ እንደሆነ ገልጿል። የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ እየተደረገ ላለው ጥረት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ድርጅቱ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።