በሶማሌ ክልል በሊበን ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የዉሃ-ወለድ ተላላፊ ወረርሽኝ ተከሰተ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2008)

በሶማሊያ ክልል እየተባባሰ የመጣዉን የድርቅ አደጋ ተከትሎ በሊበን ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የዉሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ አስታወቀ።

በሽታዉን ለመቆጣጠርም የተለያዩ የጤና ተቋማት ርብርብን እያደረጉ እንደሚገኙና ወረርሽኙ ወደ ተጎራባች ዞኖች ለመዛመት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ድርጅቱ ገለጿል።

ባለፈዉ ወር ተመሳሳይ ወረርሽኝ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አካባቢ ተቀስቅሶ የነበር ሲሆን፣ በጤና ድርጅቶች በተደረገ ርብርብ ወረርሽኙ ያደረሰዉ ጉዳት እየቀነሰ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት አመልከቷል።

ይሁንና ወረርሽኙ በሶማሊ ክልል በአዲስ መልክ መቀስቀሱ የተላላፊ በሽታዎች ስጋት እያጨመር መመጣቱን አመላካች እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል።

የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በሀገሪቱ ተከስቶ ያለው የድረቅ አደጋ ለተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ መቀስቀስ መንስኤ ይሆናል በማለት የጤና ባላሙያዎችን አሰማርቶ እንደሚገኝ አስታዉቋል።

በኢትዮጵያ ያለዉ የጤና መሰረተ ልማት በሽታዉን ለመቋቋም የሚያስችል ባለመሆኑ አለም አቀፍ ተቋማት በጤና ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸዉ የጤና ድርጅቱ አሳስቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በድርቁ ምክንያት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ አስታዉቋል።

ለተረጂዎች የሚፈለግዉ የምግብ ድጋፍ እስከቀጣዩ ወር ድረስ ወደ ሀገሪቱ የሚደርስ ካልሆነም ጉዳዩ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ ባወጣዉ ሪፖርት ገልጿል።

ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት ድጋፍ በመዘግየቱ ድርቁ እያደረሰ ያለዉ ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን ደግሞ አለም-አቀፍ የእርዳታ ተቋማት አመላክተዋል።

መንግስት በበኩሉ ተከስቶ ያለዉን አደጋ ለመቋቋም 70ሺ ቶን ስንዴ ለመግዛት አለም አቀፍ ጨረታ ማዉጣቱንና የስንዴ ግዢዉ ወጪ በአለም አቀፍ ባንክ እንደሚሸፈን ሮይተርስ ዘግቧል።

ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎችን ለመደገፍም 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን የተረጂዎች ቁጥር በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ዉስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ተብሎ ተተንብዮአል።