(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 23/2011) በጄነራል አብረሃም ወልደማርያም ኳርተርና በጄነራል ገብሬ ዲላ የታቀደው ቀውስ መክሸፉን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ አቶ ሙስጠፋ ዑመር ለኢሳት እንደገለጹት በህወሀት ጄነራሎች የሚመራው የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ኔትወርክ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተደርሶበታል።
ሰሞኑን በእነዚሁ የህውሀት ጄነራሎች አስተባባሪነት በተፈጠረ ቀውስ የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ለማወቅ ተችሏል።
በጄነራል አብረሃምና ጀነራል ገብሬ የሚመራው ኔትወርክ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎችን ይዞ ለውጡን ለመቀልበስ የተዘጋጀ ቢሆንም የክልሉ መንግስት በወሰደው እርምጃ እቅዱ መክሸፉን አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።
በቀውስ ፈጣሪ ኔትወርክ ውስጥ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ እናት እንደሚገኙበትም ታውቋል።
ከጂጂጋ ሰሞኑን የሚሰማው ነገር ጥሩ አልነበረም።
ኢሳት ወደ አካባቢው በመደወል ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በወሰደው ርምጃ አንድ ሰው መገደሉን ተከትሎ ስጋት ውስጥ ገብተዋል።
በሌሎች አከባቢ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ዳግም ሊፈጸም ይችላል በሚል ህዝቡ በቤተክርስቲያን አካባቢ መሰባሰቡን ነው ያነጋገርናቸው የሚገልጹት።
የሰሞኑ ቀውስ መነሻው የተደራጁና ገንዘብ የተከፈላቸው ወጣቶች በሌሎች አካባቢ ተወላጆች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ሲሆን የክልሉ ፕሬዝዳንት በግል ገጻቸው የዘር ጥቃት በክልላችን ቦታ የለውም ሲሉ አውግዘዋል።
በጂጂጋ የተፈጠረውን የሰሞኑን ቀውስ በተመለከተ ኢሳት ያነጋገራቸው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ጄነራል አብረሃም ወልደማርያም ኳርተርና ጄነራል ገብሬ ዲላ የሚመሩትና ለዓመታት በኮንትሮባንድ ንግድ የተሳሰረው ኔትወርክ ከቀውሱ ጀርባ እጁ አለበት ብለዋል።
እነዚህ የህወሃት ጄነራሎች ከቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ተከታዮች ጋር በመሆን በሶማሌ ክልል የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ እቅድ ነድፈው እየሰሩበት መሆኑ ተደርሶበታል።
አቶ ሙስጠፋ እንደሚሉት ጄነራሎች የሚመሩት የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ኔትወርክ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን አሰማርተው የሰሞኑ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል።
ከ10ሺህ እስከ 50ሺ ብር ድረስ ለተደራጁት ወጣቶች በተናጠል ገንዘብ መመደቡም ታውቋል።
የአብዲ ዒሌ ወላጅ እናትም በዚሁ ቀውስ ውስጥ እጃቸው እንደሚገኝበት ነው አቶ ሙስጠፋ የገለጹት።
የህወሃት ጄነራሎች በሶማሌ ክልል የኮንትሮባንድ ንግድ ከፍተኛ ሀብት ያካበቱ መሆናቸው ይነገራል።
ከሶማሌ ላንድ በጂጂጋ በኩል እስከ ጁባ የተዘረጋውን የኮንትሮባንድ ንግድ የሚመሩት ጄነራል አብረሃም ወልደማርያም ኳርተርና ጄነራል ገብሬ ዲላ ከአብዲ ዒሌ መታሰር በኋላ በክልሉ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውም ታውቋል።
አቶ ሙስጠፋ እንደሚሉትም እነዚህ ጄነራሎች አሁንም በሶማሌ ክልል ውስጥ ሆነው በጥቅም ከተሳሰሯቸው ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ጋር በመሆን ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ ቆይተዋል።
የክልሉ መንግስት የእነዚህ ለውጥ ቀልባሾች እቅድ ለማክሸፍ ርምጃ መውሰዱን የገለጹት አቶ ሙስጠፋ ከግጭቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ሰዓት በጂጂጋም ሆነ በመላው የሶማሌ ክልል አካባቢ ያንዣበበው አደጋ መቀረፉን የተናገሩት አቶ ሙስጠፋ የጄነራሎቹና የአብዲ ዒሌ የሽብር ዕቅድ ከሽፏል ብለዋል።