ኢሳት (ሰኔ 19 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን በያዝነው ሰኔ ወር ብቻ 67 ሕጻናት በረሃብ መሞታቸውን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ሰኞ ይፋ አደረገ። 51 ህጻናት የሞቱት ወሩ በገባ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ዞን ያለው የረሃብ ሁኔታ አስደንጋጭ ሆኖ መቀጠሉን ያስታወቀው የፈረንሳይው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን 27 የመመገቢያ እንዲሁም አራት የህክምና እና የመመገቢያ ጣቢያ በማቋቋም ከመንግስት ጋር በትብብር መስራቱን ቢቀጥልም ችግሩን መቆጣጠር አለመቻሉን አስታውቋል።
በዚህ በዶሎ ዞን ገላዲ እና ዲኖትን ጨምሮ በ50 ወረዳዎች ከጥር ወር ጀምሮ እድሜያቸው ከ5 አመታት በታች ለሆኑ 6ሺህ 136 በረሃብ ለተጎዱና ለሞት የተጋለጡ ህጻናት ህክምና እና የተመጣጠነ ምግብ ማቅረቡን ገልጾ ይህ አሃዝ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ10 እጥፍ መጨመሩን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታውቋል። የአምናው የተመሳሳይ ወቅት አሃዝ 491 ብቻ እንደነበርም አስታውቋል።
ችግሩ እየተባባሰ በመቀጠሉ በርሃብ የተጎዱና ለአደጋ የተጋለጡ 322 ህጻናት በሰኔ ወር ብቻ መቀበሉን ጠቁሞ ከነዚህ ውስጥ ሃምሳ አንዱ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ህይወታቸው አልፏል። በአጠቃላይ በሰኔ ወር በዶሎ ዞን በረሃብና በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሞቱ ህጻናት ቁጥር 67 መድረሱንም ሜዲሲን ሰን ፍሮንቴርስ ማለትም ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ድረ-ገጽ አስፍሯል።
በመንግስት በኩል በቀን ከሁለት እስከ ሶስቴ የበሰሉ ምግቦችን በየካምፑ ማድረስ የቀጠለ ቢሆንም ምግቡ በቂ አለመሆኑና ይህም በመቆሙ ያልበሰሉ ምግቦች ማቅረብ መቀጠሉን ከድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ዘገባ መረዳት ተችሏል። በዚህም ረገድ የሚታደለው ምግብ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ጨርሶ ምግብ እያገኘ አለመሆኑም ተመልክቷል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም እንዳስጠነቀቀው አስቸኳይ የምግብ አቅርቦቱ በአንዳንድ የሶማሊያ አካባቢዎች እስከ ሃምሌ መጨረሻ ድረስ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚሆን የሶማሌ ክልል ህዝብ ለአደጋ ይጋለጣል።