(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2010)
በሶማሌ ክልል ከሚገኘው ጄል ኦጋዴን እስር ቤት በይቅርታ ተፈቱ የተባሉ ከ1500 በላይ እስረኞች ተመልሰው ወደ እስር ቤት እንዲገቡ መደረጉ ተገለጸ።
ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ሽፋን የሰጡት የፍቺ ዜና ሳምንት ሳይሞላው እስረኞቹ ወደ ጄል ኦጋዴን ገብተዋል ያለው የሶማሌ ክልል ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ መገናኛ ብዙሃኑ በአስቸኳይ የሰሩትን ዜና እንዲያስተባብሉ ጠይቋል።
እስረኞቹ መፈታታቸው ተገልጾ፣ ፎግራፍና ቪዲዮ ከተቀረጹና ዜና ከተሰራጨ በኋላ የዚያኑ ዕለት ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን የአክቲቪስቶቹ መረብ ለኢሳት በላከው መረጃ ላይ ተገልጿል።
ጄል ኦጋዴን በሶማሌ ክልል ጂጂጋ አቅራቢያ የሚገኝ ከሀረር ከተማ በ80ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ እስር ቤት ነው።
ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምበት እስር ቤት በመሆኑ በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ‘’የሰቆቃ ማዕከል’’ በሚል እንደሚጠራ ይነገራል። ከጄል ኦጋዴን ገብቶ በህይወት መትርፍ የማይታሰብ ይላሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዲሪዬ። ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከጄል ኦጋዴን ከ1500 በላይ እስረኞች መለቀቃቸው ሲሰማ ለብዙዎች ያልተጠበቀ ዜና ሆኖ ነበረ።
የሶማሌ ክልል መንግስት የተፈቱትን እስረኞች በሰልፍ ደርድሮ፡ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ጋብዞ የእስረኞቹን መፈታት ሲገልጽ ለቤተሰቦቻቸው ትልቅ ደስታ እንደነበረ በወቅቱ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከሮይተርስ በተጨማሪ ኤኤፍፒ ፡አልጀዚራ፡ ቢቢሲና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ዜናውን ሽፋን ሰጥተው አሰራጭተውታል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይፋ መሆን ሶስት ቀናት በኋላ እስረኞቹ በይቅርታ መፈታታቸው ተገልጾ የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ በባለስልጣናት ሲገለጽ ቆይቷል። ይህ በሆነ ዕለት ለቤተሰብ ጥሩ ያልሆነ መረጃ ደርሰ። ተፈቱ የተባሉት እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው ይቀላቀላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ዳግም ወደ ጄል ኦጋዴን ገብተው የእስር ጊዜያቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑን ነው የሶማሌ ክልል ተወላጆች የአክቲቪስቶች መረብ ለኢሳት በላከው መረጃ ያስታውቀው።
የመረቡ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዲሪዬ እንደሚሉት የሚዲያ ሽፋን ከተሰጠውና ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ አግኝተናል ብለው ካመኑበት በኋላ ተፈቱ የተባሉትን በሙሉ ወደ ጄል ኦጋዴን ተመልሰው ገብተዋል። የቤተሰብ አባላት ባልስልጣናትን ለማነጋገር ሞክረው የሚፈታ ሰው እንደሌለ እንድተነገራቸው አቶ ጀማል ገልጸዋል። የሶማሌ ክልል ተወላጆች የክቲቪስቶች መረብ ጉዳዩን ለዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳውቁንም የደርሰን መረጃ አመልክቷል። የፍቺ ድራማውን የዜና ሽፋን የሰጡት ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች በአስቸኳይ ማስተካከያ አድርገው እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ አቤቱታ እንዲደርሳቸው መደረጉም ተገልጿል። አቶ ጀማል እንዳሉት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ እስረኞችን ወደ ጄል ኦጋዴን ባስገባበት በዚህ ሳምንት ላልተፈቱ ሰዎች ዜና የሰሩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የሚዲያ ስነምግባርን ተከትለው የሰሩትን ዜና በአስቸኳይ እንዲያስተካክሉት የሚጠይቅ ዘመቻ ተከፍቷል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከሶማሌ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።