ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2008)
በቅርቡ በሶማሊ እና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች የተከሰተው ውሃ ወለድ ተላላፊ ወረርሽን በሽታ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስከኞ አስታወቀ።
የድርቁን አደጋ ተከትሎ በተከሰተው በዚሁ ወረርሽን በኦሮሚያ ክልል ቦረና እና በሶማሌ ሊበን ዞን በሚገኙ ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በወረርሽኙ ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
የወረርሽኙ ስርጭት ወደሌሎች ወረዳዎችና ክልሎች እንዳይዛመት ለማድረግም ከእርዳታ ሰጪ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ርብርብ እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎችን ህይወት ለመታደግም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።
ይኸው በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ በብዙ ሺ በሚቆጠሩ ተረጂዎች ላይ የጤና ችግርን ያስከትላል ተብሎም ተሰግቷል።
የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት ሊቀሰቀስ የሚችል የበሽታ ወረርሽኝ የመቋቋም አቅሙ አናሳ በመሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ቡድንን በማሰማራት የበሽታ ወረሽኞች እንዳይዛመቱ ድጋፍን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በምግብ እጥረት ላይ ካስከተለው ተፅዕኖ በተጨማሪ የጤና ቀውስን ያስከትላል ተብሎ ስጋት መኖሩንም የጤና ድርጅቱ አመልክቷል።
ከውሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት በተጨማሪ በቆዳ ላይ የሚከሰት የእከክ በሽታም በድርቅ አደጋ በተጎዱ የአማራና የትግራይ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ የተከሰተ ሲሆን የእርዳታ ተቋማትና መንግስት የመድሃኒት አቅርቦት ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መረጃ ድርጅት በበኩሉ በድርቁ ክፉኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ የግማሽ ሚሊዮን ህጻናት ወደአሳሳቢ ደረጃ እየተሻገረ መምጣቱን በድጋሚ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ከእነዚሁ ተረጂዎች መካከል አምስት ሚሊዮን የሚልቁት ህጻናት መሆናቸው ተገልጿል።
ለምግብ ድጋፍ ከተጋለጡት ህጻናት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ክፉኛ የምግብ እጥረት በአካላቸውና በጤናቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የህጻናት መረጃ ድርጅቱ አስታውቋል።