በሶማሊ ክልል አብዲ ኢሌን በመቃወም የሚደረጉ ሰልፎች ቀጥለዋል

በሶማሊ ክልል አብዲ ኢሌን በመቃወም የሚደረጉ ሰልፎች ቀጥለዋል
(ኢሳት ዜና ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ/ም) በሊበን ዞን በዶሎ አዶ ትናንት የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ አብዲ ኢሌ ሚሊሺያዎቹን በማዘዝ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን የአካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል። ተቃውሞውን ለመበተን ልዩ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ እስካሁን ድረስ 3 ሰዎች መገደላቸውንና ከ10 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተወላጆቹ ተናግረዋል።
ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ የገጠመው አብዲ ኢሌ የትኩረት አቅጣጫ ለማሳትና ችግሩን ከጎሳ ግጭት ጋር ለማያያዝ በሶማሊ ክልል በጃርሶና እና ገሪ ጎሳዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ እያደረገ ነው። ትናንት በቱሊጉሌድ ከተማ በገሪና ጀርሶ ጎሳዎች መካከል የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ተዋላጆች ይናገራሉ።
የህወሃት ነባር አመራሮች አብዲ ኢሌ ከስልጣን እንዲነሳ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙትን የአገር ሽማግሌዎች- ከአብዲ አሌ ጋር ለማስታረቅ እየተመላላሱ ቢሆንም ዛሬም አልተሳካለቸውም። በአንድ በኩል የሽምግለና ጥረት እየተደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ግድያውና እስሩ ተጠናክሮ መጠሉን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ አብዲ ኢሌ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የፌደራል ባለስልጣናት እንዲደግፉት የማሳመን ስራ እየሰራ ነው።
በኢህአዴግ ውስጥ ከአብዲ አሌ ገንዘብ ያልተቀበለ ነባር አመራር እንደሌለ የሚገልጹት ምንጮች፣ አሁንም ድረስ ብዙ ባለስልጣናት አብዲ ኢሌ በስልጣን እንዲቆይላቸው ይፈልጋሉ ብለዋል። ከህወሃት ጄኔራሎችና ነባር አመራሮች በተጨማሪ እነ አምባሳደር ካሳ ተክለ ብርሃን፣ ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚዓብሄርና ጌታቸው አምባዬ የአብዲ ኢሌ ተከፋዮች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በዚህም የተነሳ አብዲ አሌ በክልሉ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ሲፈጸም አይተው እንዳላዩ ሲያልፉት መቆየታቸውንና አሁንም አዲሱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይህንኑ አካሄድ እንዲከተል ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን የቅርብ እማኞች ተናግረዋል