በሶማሊያ ክልል 47 ሰዎች መገደላቸውን የአገር ሽማግሌዎች ለአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በላኩት ደብዳቤ ገለጹ

ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቀላፎ አካባቢ የሚኖሩ የየረር ባሬ ጎሳ  የአገር ሽማግሌዎች ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገቡትና መረጃው ለኢሳት እንዲደርስ በሚል በላኩት መረጃ ፣ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሀም በቅጽል ስማቸው ኳታር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ሀይል ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን መግደሉን የሟቾቹን ስም ዝርዝር በመጥቀስ ገልጸዋል።

ልዩ ሚሊሺያው ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንዳሉ ተኩስ መክፈቱን የአገር ሽማግሌዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ደርሶ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።

የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የክልሉ መንግስት ጭቆና ያደርስብናል በማለት ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ሲጠይቁና በተደጋጋሚ እርምጃ ሲወሰድባቸው እንደነበር አውስተው ፣ በቅርቡ የተወሰደው አስከፊ እርምጃ ግን በደቡብ አፍሪካ እንሰማው የነበረ እንጅ በአገራችን ላይ የሚፈጸም ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል ብለዋል።

ባከፍ ድር እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ላይ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በተከፈተው ተኩስ  ኡመር ሀጂ ሙሀመድ፣ ሙኒየር አዳቢ ሙሀመድ፣ ካሊድ ሙሀመድ አብዲ፣ ሀሰን አሊ ቤላህ፣ ወ/ሮ ሀሺ ሃጅ መሀመድ፣ ማዴቦ ሞሀመድ አብዲ፣ ሀጂ ኑሩ  ሙሀመድ፣ ማዴባ ሞሀመድ አብዲ፣ መሀለም ካልየ ደውሀሊ፣ አብረሳ አደም ሞሀመድ፣ ሀጂ ኑሩ ሙሀመድ፣ ሞርየ ሞሀመድ ካር፣ ጋለው አብዲ የኑስ፣ የሱፍ ረምሳ አደም፣ ካሊባን ሳራህ ኡመርነህ፣ ኡስማን  አብደሌ፣ ጠኒ ሙሀመድ ጣር፣ መንሲን ሙሀመድ ጣር፣ ደልግ አሊ ኡመር፣ ካሊድ ሙሀመድ አብደሌ፣ ሀሰን ማሌ አብዱላሂ፣ የሱፍ የሄ፣ ጀማል ኡመር ጠባህ፣ ሙሀመድ ኡስማን ጦለቤ፣ አህመድ መሀመድ፣ አሊ ቀሲም ቀለኔ፣ ባቡል ዳሩር፣ ከሬ ባዴ፣ ማን ኦረየ ባዴ፣ ጦርየ አዊ ባዴ፣ አብዲ ሸክለሌ፣ አሊ ኡስማን ቀለሌ፣ ሊሞ አሌባዴ፣ ማዲህ አብዱልኑር፣ ዙቅ ኡር እና የሌሎች የ12 ተጨማሪ ሟቾች ስም ዝርዝር ቀርቧል።

በአካባቢው የተነሳው ውጥረቱን ተከትሎ በትናንትናው አለት ደግሞ ተጨማሪ ሀይል ወደ አካባቢው መጓዙን ሽማግሌዎች ገልጸዋል።

ክልሉን ከጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት ጄኔራል አብርሀ በክልሉ ለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ መሆናቸውን የአካባቢው ሰዎች ይገልጻሉ።

መረጃው እንደተላከልን የክልሉን ፕሬዚዳንት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም። ጠ/ሚንስትሩ ለተጻፈላቸው ደብዳቤ እስካሁን መልስ አለመስጠታቸውን ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል።

የሶማሊ ክልል በቅርቡ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ማክበሩ ይታወሳል።