ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)
በቅርቡ በሶማሊያ ክልል በሚገኘው የጃማ ዱባብ የገጠር መንደር አካባቢ ተቀስቅሶ ለ21 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት ዳግም ተቀሰቀሰ።
አካባቢውን ከሶማሌላንድ ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰው ይኸው ግጭት ጎርጎር፣ አሊ ቡራሌ እና ቦዴ ድሂር በሚባሉ ሶስት የገጠር መንደሮች መዛመቱን የሶማሊላንድ ፕሬስ ሃሙስ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።
ከሁለት ቀን በፊት በሶማሊ ክልል ልዩ ሃይሎች እየተወሰደ ነው በተባለው በዚሁ ጥቃት ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ የአካባቢው ነዋሪዎች መሞታቸውንና ለእስር መዳረጋቸውን እማኞች ገልጸዋል።
በአካባቢው ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በጸጥታ ሃይሎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ተከትሎ በስፍራው ግጭት መቀስቀስ መጀመሩን የተናገሩት ነዋሪዎች በትንሹ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አክለው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደነጻ አገር አድርጋ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ጠንካራ የድንበር ንግድ ልውውጥ ያላት አገር ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ በተደጋጋሚ የሚቀሰቀሰውን ግጭት የሶማሊላንድ ባለስልጣናት በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዳቸው ይታወሳል።
ይሁንና ጉዳዩ ዕልባት አለማግኘቱን ያስታወቁት የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን ለሶማሊላንድ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ የድንበር አካባቢ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።
ከቀናት በፊት በድንበሩ አካባቢ የተቀሰቀሰን ይህንኑ አዲስ ግጭት ተከትሎ ሃውድ ተብሎ በሚጠራ የሶማሊላንድ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸን ሶማሊላንድ ፕሬስ ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
በግጭቱ ዙሪያ ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።