ኅዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢዎች በኮሌራ በሽታ 35 ሰዎች መሞታቸውንና ድርቁን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑን የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት አስታወቀ። በድርቁ ምክንያት እንስሳት እየሞቱ ነው። የምግብ እጥረት ተጠቂ የሆኑት የኦጋዴን ነዋሪዎች አፋጣኝ እርዳታ ካላገኙ አደጋው የከፋ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ለጋሽ የረድኤት ድርጅቶች ለነዋሪዎቹ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ እገዛዎች እንዳያሰራጩ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮችና የአካባቢው ሚሊሻዎች ሳንካ እየፈጠሩባቸው ነው። ወታደሮቹ እና የክልሉ ታጣቂዎች ሕዝቡ በርሃብ እየረገፈ እርዳታዎችን በመዝረፍ በሕገወጥ መንገድ የኮንትሮባንድ ሽያጭ ላይ ተሰማርተዋል። በኦጋዴን የተከሰተው ርሃብ ሰውሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋ መሆኑ ሲታይ ሁኔታውን ይበልጥ ውስብስብና አሳሳቢ አድርጎታል።
በኦጋዴን የተከሰተውን የኮሌራ ወረሽኝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ እንዳይታወቅ የኢትዮጵያ መንግስት መሸፋፈኑን አሁንም ገፍቶበታል ሲል ግንባሩ አስታውቋል። እስካሁን ድረስ በክልሉ መንግስትም ይሁን በፌደራል መንግስት በኩል ትርጉም ያለው እንቅስቃሴዎች አልተደረገም የሚለው ግንባሩ፣ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው እልቂትን ለመታግ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪውን አቅርቧል።
በክልሉ የኮሌራ ወረሽኝ መዛመቱን እና ድርቁ በፈጠረው የዝናብ እጥረት ምክንያት በደቡባዊ ምስራቅ ኢትዮጵያ አዲስ የድርቅ አደጋ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ በአርብቶ አደሮች ላይ መጠነሰፊ የርሃብ አደጋ ማንዣበቡን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ጉዳይ ባሳለፍነው ሳምንት አስጠንቅቋል።
በአፋር ክልል በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ህጻናትና በእድሜ የገፉ ነዋሪዎች ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን ኢሳት ከቀናት በፊት ዘግቧል።