በሶማሊያ ከ100 በላይ ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 27 ፥ 2009)

ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ በረሃብ ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች በሶማሊያ መሞታቸውንና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ እንደሚካሄድ ስጋት መኖሩን የሃገሪቱ ባለስልጣናት ሰኞ ይፋ አደረጉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎረቤት ሃገራት ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ የከፋ ችግር ከማስከተሉ በፊት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ በድጋሚ አሳስቧል። በዚሁ የድርቅ አደጋ ተጠቂ በሆነችው ሶማሊያ ቤይ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ባለፉት ሁለት ቀናቶች ብቻ 110 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።

የሃገሪቱ መንግስት ባለፈው ሳምንት የድርቅ አደጋ ብሄራዊ ቀውስ እንደሆነ ካወጀ በኋላ የምግብ እጥረቱ በሰዎች ላይ የሞት አደጋን ሲያስከትል ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሊያ ወደ 5 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጣቸውንና ድርቁ ወደ ረሃብ ደረጃ በመሸጋገር ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን አስታውቋል። በኢትዮጵያ፣ የመን፣ ኒጀርና ደቡብ ሱዳን ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋም እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል።

በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን ያስታውቀው ድርጅቱ በክልሉ ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደሚገኙ አውስቷል።

በኢትዮጵያ አዲስ በተከሰተው በዚሁ የድርቅ አደጋ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ድጋፍ እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

በሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በመባባስ ላይ መሆኑን ተከትሎ ተረጂዎች በመጠለያ ጣቢያ እንዲሰባሰቡ ተደርጎ የዕርዳታ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን መንግስት ገልጿል።

ይሁንና የእርዳታ ድርጅቶች ተረጂዎች ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ በማስታወቅ ችግሩ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በማሳሰብ ላይ ናቸው። በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾና ሌሎች ግዛቶች የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በመጠለያ ጣቢያዎች እየተሰባሰቡ መሆኑንም አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ወደ 400ሺ የሚጠጉ ህጻናት በምግብ እጥረቱ ሳቢያ ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ ህይወታቸውን የሚያጡ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ተሰግቷል።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብዱላሂ የአለም አቀፉ ማህበረሰብና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የሃገሪቱ ዜጎች የተቻላቸውን ሁሉ ርብርብ በማድረግ እየደረሰ ያለውን የሰዎች ህይወት መጥፋት እንዲታደጉ ጥሪን አቅርበዋል።