ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)
በቅርቡ በሶማሊና አፋር ክልሎች የደረሰው የጎርፍ አደጋ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የእርዳታ አቅርቦት እንዳይደርስ ተፅዕኖ መፍጠሩን የእርዳታ ተቋማት ሰኞ አስታወቁ።
ከ20 ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ የነበረው የጎርፍ አደጋ በርካታ የትራንስፖርት መሰረተ-ልማቶችን በማውደሙ የእርዳታ እህል ለተረጂዎች እየደረሰ እንዳልሆነ የኖርዌይ የስደተኞች ኮሚሽን ገልጿል።
በሶማሊ ክልል የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ሞሃመድ ሃሰን ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተገኘለት በርካታ ነዋሪዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ሲሉ ለሮይተርስ አስረድተዋል።
በቅርቡ በጅጅጋ ከተማ ዙሪያ የጣለን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በከተማዋ በትንሹ 28 ሰዎች መገደላቸውና ከ50 የሚበልጡትም የገቡበት አለመታወቁ ይታወሳል።
በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በሶማሊያና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ በክልሉ በሰብዓዊ እርዳታ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይሁንና በቅርቡ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ውሃ ወለድ በሽታዎችን በመቀስቀስ በተረጂዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳትን ያደርሳል ተብሎ ተሰግቷል።
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በበልግ ወቅት ይጥላል ተብሎ የተጠበቀው ዝናብ በአግባቡ ባለመጣሉም የድርቁ አደጋ እስከ ቀጣዩ አመት ድረስ ዘላቂ ሊሆን ይችላል ተብሎ መጠበቁንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ለተረጂዎች የሚፈለገው ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይም በታሰበው መጠን አለመገኘቱ ድርቁን በመከላከሉ ስራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ድርጅቱን አክሎ ገልጿል።