በሶማሊላንድ የአማራና ኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ተያዙ

ጥር ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን ከ250 ያላነሱ የአማራ እና ኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በሶማሊላንድ ፖሊሶች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ ከእስሩ ጀርባ የህወሃት ኢህአዴግ መንግስት እጅ እንዳለበት ታውቋል።
የኦነግ እና የአርበኞች ግንቦት7 ወኪሎች በሶማሊላንድ መኖራቸውን መረጃ ደርሶናል በሚል የህወሃት/ኢህአዴግ የደህንነት አባላት ከሶማሊላንድ የጸጥታ አባላት ጋር በመሆን የተያዙት ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲተላለፉ እየጣሩ ነው። ብዙዎቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኝነት ወረቀት አላቸው።
ምንጮች እንደሚሉት በሶማሊላንድ የሚገኙ 4 የህወሃት አባላት የነበሩ ጡረታ የወጡ የጦር መኮንኖች ጀልባዎችን ገዝተው ከፍተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ሰዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያሻግራሉ። እነዚህ ሰዎች በአገሪቷ የሚገኙከ3 ሺ ባላነሱ ኢትዮጵያውያን ላይ ክትትል የማድረጉንም ስራ በሃላፊነት ወስደው ይሰራሉ። አሁን በእስር ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን እስር ጀርባም የእነዚህ ሰዎች እጅ እንዳለበት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይገልጻሉ።
በቅርቡ በሶማሊ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ ላይ ተደርጎ በነበረው የደህንነት አባላት ስብሰባ ላይ ፣ በሶማሊላንድ የሚገኙ የመንግስት ተቃዋሚዎች እየተፈለጉ እንዲያዙና ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ ውሳኔ ተላልፎ ነበር።