በስድስት ክልሎች የሚገኙ 26 ወረዳዎች ወደ ረሃብ ደረጃ መሸጋገራቸው ተነገረ

ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ መባባስን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ተመድበው የነበሩ 26 ወረዳዎች ወደ ረሃብ ደረጃ ሊሸጋገር ወደሚችለው አንደኛ ደረጃ መሸጋገራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

ወደ አንደኛ ደረጃ የተሸጋገሩት እነዚሁ ወረዳዎች ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ጭምር ክፉኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብሎ ስጋት መኖሩን ድርጅቱ በሃገሪቱ ስላለው የድርቅ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መሻሻልን ባለማሳየቱ ምክንያት አሁንም ድረስ 206 ወረዳዎች በአንደኛ ደረጃ ተፈረጀው የሚገኙ ሲሆን፣ ተጨማሪ 154 ወረዳዎች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

በቅርቡ ወደ አንደኛ ደረጃ የተዘዋወሩት 26 ወረዳዎች የኮሌራ በሽታን ጨምሮ በወባና በሌሎች ተላላፊ ወረርሽኞች ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል የተባበሩት መግንስታት ድርጅት አመልክቷል።

ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ 10.2 ሚሊዮን ሰዎች የሚያስፈልገው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሙሉ ለሙሉ ሊገኝ ባለመቻሉ ምክንያት ድርቁን የመከላከሉ ስራ የተጠበቀውን ውጤት ሊያመጣ አለመቻሉን የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ እስከቀጣዩ ወር ድረስ የ700 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ገልጿል።

ድርቁ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ የሚያፈናቅላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት በእርዳታ ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን አሳድሮ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።

እስከ ባለፈው ሰኔ ወር ድረስ ብቻ በሃገሪቱ በጎርፍ አደጋ ከ 630ሺ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ የክረምቱ ወር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ጭምር በከፍተኛ መጠን መጨመርን ያሳያል ተብሎ ተሰግቷል።

ወደረሃብ ደረጃ ለመሸጋገር አንድ ደረጃ ብቻ ይቀራቸዋል የተባሉት 206 ወረዳዎች የሚያስፈልጋቸው የእርዳታ አቅርቦት በአግባቡ የማያገኙ ከሆነ፣ በወረዳዎቹ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች በማሳሰብ ላይ ናቸው።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርጅቶቹ እየሰጡ ያለው ማሳሰቢያ የተጋነነ ነው በማለት ተረጂዎችን ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።