ኢሳት (ጥቅምት 30 ፥ 2009)
በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማውገዝ የአደራ መንግስት እንዲቋቋም ጥሪ አቀረበ።
በኦሃዮ ደብረ መድሃኒት መድሃኔአለም ቤተ ክርስቲያን ከጥቅምት 23-26 2009 ባደረገው ስብሰባ በሌሎች የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ጭምር እንደተወያየ ለኢሳት የላከው መግለጫ ያስረዳል።
በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የተመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህወሃት አገዛዝ በህዝቡ ላይ በጫነው ፍጹም ወታደራዊ አገዛዝ፣ በህዝቡ ላይ ስለደረሰው ስነልቡናዊ ተጽዕኖና፣ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ውይይት መደረጉን ከወጣው መግለጫ ላይ ለማወቅ ተችሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ፣ በህዝብ ላይ ሞትን ያወጁት የህወሃት ባለስልጣናት “አዋጃቸውን በአዋጅ እንዲሽሩ ይጠይቃል፣ በህዝቡ ላይ የተላለፈውን የአፈናና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያወግዛል” ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው አስታውቋል።
ህወሃት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጋምቤላ፣ የኮንሶ በማለት የጥቃት ኢላማ በማድረግ የጥፋት ስራውን መቀጠሉን አጥብቆ ይቃወማል ሲል የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ይህ የአፈና ስርዓት እንዲለወጥ እያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ህብረት ፈጥሮ የህወሃትን እድሜ እንዲያሳጥር በአጽንዖት ጠይቋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፈው መልዕክት፣ ለህዝብና ለአገር ህልውና ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ ከብሄርና ከጎሳ ይልቅ ኢትዮጵያዊነትና አብሮነትን ማዕከል ያደረገ ስራ እንዲሰሩ ልዩነታቸውን በማቻቻል ለሃገርና አንድነት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ተማጽኖ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያን፣ የእስልምና ተቋማት ሌሎችም የዕምነት ተቋማት በህዝብና ለአገር ህልውና ሲባል በህብረት የአገር አድን ኮሚቴ እንዲያቋቁሙና በጋራ እንዲሰሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ማስተላለፉን ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ስለሃገሩ እንዲጸልይ፣ በሃይማኖት ጸንቶ በአንድነት እንዲቆም ተማጽንዖ ቀርቧል።
44ኛውን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የህወሃት ከስልጣን እንዲወገድ የሚጠይቀው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የአገር ስማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የሴቶች፣ የወጣቶች እና የሃይማኖት ተቋምት ያካተተ ጊዜያዊ የአደራ መንግስት እንዲቋቋም ጠይቋል።