በስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሩዋንዳው የደህንነት አዛዥ ተገደሉ

ታህሳስ ፳፬( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ አፍሪካ በስደት ላይ የሚገኙት የሩዋንዳ የደህንነት ዋና አዛዥ የነበሩት ፓትሪክ ካሪጋያ የተገደሉት ጆሀንስበርግ  በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ነው።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ እንዳለው የሩዋንዳ መንግስት ተቃዋሚ የሆኑት ካሪጋያ የተገደሉት በገመድ ታንቀው ሳይሆን አይቀርም።

የ53 አመቱ ሚ/ር ካሪጋያ ላለፉት 6 አመታት  በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በስደተኝነት ቆይተዋል። ኮሎኔል ካሪጋያ ከፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ከተጋጩ በሁዋላ ማእረጋቸው እንዲገፈፍ ተድርጓል።

የፕሬዚዳንት ካጋሜ መንግስት የጄኔራል ፋውሲትን ደጋፊ በሆኑት የደህንነት ሹሙ ላይ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት በጄኔራል ፋውስቲን ላይ ሁለት ጊዜ የመግደል ሙከራ አድርገዋል።

የሩዋንዳ መንግስት ባለስልጣናት ግን ግድያውን እነሱ እንዳላስፈጸሙት ይናገራሉ። የካጋሜን መንግስት የሚተቹ ሁሉ ለህይወታቸው በመስጋት አገሪቱነን ለቀው እንደሚሰደዱ ቢቢሲ ዘግቧል።