(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 3/2010)
አምንስቲ ኢንተርናሽናል በሊቢያ በአፍሪካ ስደተኞች ላይ እየተካሄደ ላለው ሰቆቃ የአውሮፓ መንግስታት ተባባሪዎች ናቸው ሲል ከሰሰ።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት የአውሮፓ መንግስታት በስደተኞቹ ላይ ለሚፈጸመው ሰቆቃ በተግባር ተሳታፊ ናቸው ብሏል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንዳወጣው ሪፖርት ከሆነ የአውሮፓ መንግስታት ስደተኞቹ ባህር አቋርጠው እንዳይመጡባቸው እዛው ሊቢያ ውስጥ ታግተው እንዲቆዩ ለአዘዋዋሪዎች፣ለታጣቂዎችና ለሊቢያ ተቋማት ገንዘብ ይሰጣሉ።
በዚህም ምክንያት ይላል የድርጅቱ መግለጫ አውሮፓ በአፍሪካውያን ላይ በሊቢያ ለሚደርሰው እንግልትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተባባሪ ነች።
አምንስቲ እንዳለው የአውሮፓ መንግስታት በሊቢያ እየተደረገ ያለውን የመብት ጥሰት ያውቃሉ።ማወቅ ብቻ ሳይሆን ይተባበራሉ ብሏል።
ድርጅቱ በሪፖርቱ ሲዘረዝር የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት በተለይም ጣሊያን በሶስት መንገድ ተባባሪ እንደሆኑ ያስቀምጣል።
የመጀመሪያው በሊቢያ ያሉ ስደተኞች ታግተው ለሚገኙበት ማጎሪያ ጣቢያዎች የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ታጋቾቹ ማቆሚያ ለሌለው እንግልትና ላልተወሰነ ጊዜ እስር ይዳረጋሉ።
ሁለተኛው ለሊቢያ የባህር ሃይል ስልጠና፣መሳሪያና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ወደ አውሮፓ በባህር እየተሻገሩ ያሉ አፍሪካውያንን በመጥለፍ ወደ ሊቢያ መልሰው በማጎሪያ እንዲቆዩ ያደርጋሉ።
ሌላኛውና ሶስተኛው ደግሞ በሊቢያ ላሉ የጎሳ መሪዎች፣የታጣቂ ቡድኖች እንዲሁም በየደረጃው ላሉ የስልጣን አካላት ድጋፍ በማድረግ ስደተኞቹ ወደ አውሮፓ እንዳያመሩ እዛው እንዲያስቀሯቸው ማበረታታቸው እንደሆነ ተጠቅሷል።
አምንስቲ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት በጣም በተጨናነቁ የማጎሪያ ጣቢያዎች እስከ 20ሺ የሚደርሱ ስደተኞች ይገኛሉ።
ድርጅቱ ያነጋገራቸው ስደተኞች እንደሚሉት ባለስልጣናት፣ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እንዲሁም ታጣቂ ቡድኖች ከፍተኛ የሆነ ሰቆቃ፣የግዳጅ ስራ፣ቤተሰቦቻቸውን በማስፈራራት ገንዘብ ማስላክ እንዲሁም ግድያ ይፈጽማሉ።
የሊቢያ ባህር ሃይል በዚህ አመት ብቻ 19ሺ452 ወደ አውሮፓ ያመሩ የነበሩ ስደተኞችን ጠልፎ ወደ ማጎሪያ መውሰዱን የአምንስቲ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ አክሎም ባለፈው ወር ወደ 50 የሚጠጉ ስደተኞች ባህር ውስጥ ሰምጠው የቀሩት በነዚሁ የሊቢያ የባህር ሃይል አባላት እንዝላልነት እንደሆነ አመልክቷል።
ስደተኞቹን የያዘችው ጀልባ ተንፍሳ በመስጠም ላይ እያለች ስደተኞቹ የነፍስ አድን ጥሪ ሲያደርጉ እነሱን ለማዳን የተጠጉት የሊቢያ ባህር ሃይል አባላት በእጃቸው ያለውን ጀልባ በተገቢው መንገድ አየር ነፍተው ባለማዘጋጀታቸው 50 የሚደርሱት አፍሪካውያን ባህር በልቷቸዋል።