መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስዊዘርላንድ ካንቶን ሴንትጋለን ነዋሪ የነበረች ኢትዮጵያዊት ራስዋን ከፎቅ ላይ በመወርወር ህይወትዋን አጠፋች
መዲና ሱሌይማን የተባለች የ28 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊት ባለፈው እሁድ ማርች 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ህክምና ስትከታተል ከነበረችበት ኡዝናህ ከሚገኘው የአዕምሮ መታከሚያ ሆስፒታል ክፍል ፮ኛ ፎቅ ዘላ በመውረድ ራስዋን ማጥፋትዋን ለማወቅ ተችሏል።
ይህች ወጣት ኢትዮጵያዊት ራስዋን ያጠፋችበት ትክክለኝ ምክንያት በውል ባይታወቅም የስደተኝነት ጥያቄዋ ምላሽ ያለማግኘት ጉዳይና በየጊዜው ስደተኞችን ለማስወጣት በሚደረገው ግፊትና ጫና በተፈጠረባት ጭንቀት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል በቅርብ የሚያውቋት ጓደኞችዋ ገልጸዋል። በሆስፒታል ከቆየችባቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል ምንም አይነት የተለየ የአዕምሮ ህውከት ችግር እንዳልነበረባትና በአጭር ጊዜያት ውስጥ የታየ ክስተት መሆኑን በቅርበት የሚያውቋት ጓደኞችዋ አክለው ገልጸዋል። የመዲና ሱሌይማን የቀብር ስነ ሥርዓት ማርች 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ በምትኖርበት ሽሜሪኮን አካባቢ የተፈፀመ ሲሆን በቅርበት የሚያውቋት ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ ሃገር በርካታ ዜጎች በስፍራው ተገኝተዋል።
በአዕምሮ ህውከት ህክምና ስር ያሉ ታካሚዎች ከፍተኛ ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባ እየታወቀ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ስድስተኛ ፎቅ ላይ ያለን ወደ በረንዳ የሚወስድ በር ክፍት ማድረግ ሆስፒታሉን ሊያስጠይቅ የሚያስችል ሥህተት መሆኑን በመገመት ይመስላል ይህንን አሳዛኝ ዜና ምንም ዓይነት የመገናኛ ብዙሃን እንዲዘግበው እንዳልተደረገና እንዲደበቅ የተፈለገ መምሰሉን መረዳት ተችሏል ተስፉ ወልደሥላሴ ከስዊዘርላንድ ዘግቧል
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide