(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 29/2010)በሴራሊዮን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው።
ሴራሊዮናውያንም አዲስ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
አዲስ የሚመረጠው ፕሬዝዳንት ያቺን ሃገር ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት ብዙ ስራ ይጠብቀዋል ተብሏል።
የሴራሊዮኑ ፕሬዝዳንት እርነስት ባይ ኮሮማ ላለፉት 5 አመታት በስልጣን በመቆየታቸው የሀገሪቱ ህገመንግስት ለድጋሚ ምርጫ እንዲወዳደሩ አይፈቅድላቸውም ያላል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ፍራንስ 24።
በምትካቸውም ኦል ፕዩፕልን የተባለውን የገዢው ፓርቲ በመወከል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሙራ ካማራ እንደሚወዳደሩ ታውቋል።
3.1 ሚሊየን ድምጽ ሰጪ ተመዝግቦበታል በተባለው በዚህ ምርጫ እስከ ምሽት 12 ሰዐት ድረስ በምርጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ሰልፍ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።
ለተቃዋሚው የሴራሊዮን ፓርቲ ኤስ ኤል ፒፒ የሚወዳደሩት ጁሊየስ ማዳም ምርጫው በእስካሁኑ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን መግለጻቸው ታውቋል።
ምርጫው በዚሁ መንገድ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ ከተጠናቀቀ ውጤቱን በጸጋ እንደሚቀበሉ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል ።
በብዙሃኑ ሲራሊያውያን ዘንድ ያሸንፋሉ የሚል ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አንዱ ጁሊየስ ማዳም ናቸው።
በእስካሁኑ ሂደት ግን የገዢውን ፓርቲ በመወከል የሚወዳደሩትና በሙስና በስፋት ስማቸው የሚነሳው ሳሙራ ካማራ በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ የምርጫውን ተአማኒነት እንዳያጠፋውና በሃገሪቱ ሌላ ውዝግብን እንዳይፈጥር ከወዲሁ ስጋትን ጭሯል።
አጠቃላይ የምርጫው ውጤቱም በ 2 ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚሆንም ታውቋል።
ያም አለ ይህ ግን ለዛች ሃገር ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚመረጠው ሰው ሃገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ የማውጣት ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።
ሴራሊዮን ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች እንደ አውሮፓውያኑ ከ1961 ጀምሮ ላለፉት 57 አመታት በ 2ቱ ፓርቲዎች ስትመራ ቆይታለት።
በወጪንግድ ገቢ ላይ ኢኮኖሚዋን የመሰረተችው ሴራሊዮን ከአፍሪካ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት በቀደምትነት ትጠቀሳለች።