ግንቦት ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በሳውድ አረቢያ ለአመታት በጉልበት ስራ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በቂ አገልግሎት እየሰጠን አይደለም ብለዋል። ለተመላሽ ኢትዮጵያውያን የትራንስፖርት አገልግሎት ከማመቻቸት አንስቶ እቃዎቻቸውን ከቀረጽ ነጻ የሚያስገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው በመንግሰት መገናኛ ብዙሃን ሲገለጽ ሰንብቷል። የተለያዩ የኢህአዴግ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ከዚህ ቀደም በተመለሱት ዜጎች ላይ የደረሰው ችግር እንዳይደርስ ፣ ኢትዮጵያውያን የ90 ቀናቱን የመውጫ ጊዜ አክበረው እንዲጠቀሙ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ግን በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርበውና መሬት ላይ አለው ነገር ተለያይቶብናል በማለት እያማረሩ ነው።
ኢምባሲው ስራውን በፍጥነት ሊሰራ አልቻለም፣ ዛሬም ቀጠሮ ነገም ቀጠሮ ነው የሚሉት ኢትዮጵያውያን ወደ ኢምባሲው በመመላለስ ሰርተው ያጠራቀሙትን ገንዘብ እያጠፉ ነው። የጅዳ ቆንስላ ሰራተኞች እኛ ምን እናድርግ የሚል መልስ እንዲመሰጡዋቸው የሚናገሩት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን፣ ከዚህ በፊት እንደተደረገው አሁንም ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው ቆመው ችግሮቻቸውን እንዲረዱላቸው ጠይቀዋል።
በቅርቡ በገዢው ፓርቲና በሳውድ አረቢያ መካከል ሰራተኞችን በህጋዊ መንገድ ለመላክ ስምምነት መደረሱንም ኢትዮጵያውያን፣ አሁን በአገሪቱ ባሉት ስደተኞች ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር ነው በማለት ተቃውመውታል። ሌሎች ወገኖች ደግሞ ስምምነቱ በአገሪቱ በቂ የስራ እድል እንዳለ የሚነገረውን ፕሮፓጋንዳ የሚቃረን ነው በማለት ስምምነቱን ተችተውታል። ዜጎችን በህጋዊ መንገድ እንደመሸጥ የሚቆጥሩ ወገኖችም አሉ።
ኢትዮጵያውያን የመጨረሻው የመውጫ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ጭንቀታቸውም በዚያው ልክ ከፍ እያለ ነው።
ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት መካከል አብዛኞቹ ለችግር በመዳረጋቸውና የተወሰኑትም ተመልሰው ወደ ሳውድአረቢያ በመግባታቸው፣ አሁን በግድ አገሪቱ እንዲወጡ በሚደረጉት ኢትዮጵያውያን ላይ አሉታዊ ተጽኖ ፈጥሯል። ብዙዎች ወደ አገራችን ብንመለስ የተሻለ ነገር አያጋጥመንም እያሉ ስሜታቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች እያካፈሉ ነው። የኢምባሲ ሰራተኞች ተገቢውን አገልገሎት ለምን እንደማይሰጡ የኢንባሲውን ሰራተኞች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፤ በዚህ ዙር ከ100 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።