በሳውድ አረቢያ አንድ ኢትዮጵያዊት ራሱዋን አጠፋች

መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ከ10 ወራት በላይ የሰራችበትን ደሞዙዋን ባለመስጠታቸው ከአሰሪዎቹዋ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታ የነበረችው ኢትዮጵያዊት ተማም በሚባል ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ልብሷን ቀዳ ራሱዋን በመስቀል ማጥፋቱዋን በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ እስረኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

ወርቅነሽ የምትባለዋ ሟች አስከሬን በትናንትናው እለት ምርመራ እንደተደረገበትና ፖሊሶች አስከሬኑን መውሰዳቸው ታውቋል። በዚሁ እስር ቤት ውስጥ አንዲት ወጣት ባለፉት 3 ቀናት ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ መደፈሩዋንና የጤና መታወክ እንዳጋጠማት እስረኞቹ አክለው ገልጸዋል።

ወጣቱዋ ከአሰሪዎቹዋ ጋር የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ እጇን ለፖሊስ ለመስጠት በምትሄድበት ጊዜ መደፈሯ ታውቋል። ደፋሪዎቹን በትክክል ለማወቅ ባይቻልም፣  4 ፖሊሶች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ እሰረኞች ይናገራሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ወጣቱዋ ከተደፈረች በሁዋላ ራሱዋን እንድትስትና መረጃውን እንዳታወጣ ለማድረግ  ያለፍላጎቷ መድሃኒት በፖሊስ እንዲሰጣት መደረጉ ነው።

ልጂቱ መድሃኒት መውሰዷን ተከትሎ በእስር ቤት ውስጥ ውዝግብ ተከስቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሎአል። ተማም ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ 82 ሴት ኢትዮጵያውያን ታስረው ይገኛሉ።