ህዳር ፲፱(አስራ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደገለጹት ስትርሀ እየተባሉ በሚጠሩ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ።
በውሀ እና በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ እርጉዝ ሴቶች፣ ህጻናትና እናቶች አሁንም የድረሱልን ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው። በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊን ምግብ እና ውሀ ለመግዛት ወጣ ሲሉ እንደሚገደሉ ጓደኞቻቸው የተገደሉባቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል
የኢሳት የአዲስ አበባው ዘጋቢ እንደገለጸው ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት በአይ ኦ ኤም ወጪ ህክምና እየተሰጣቸው ሲሆን ብዙዎች ከአካል ጉዳት በተጨማሪ ለስነልቦና ቀውስ መዳረጋቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳውዲ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ለመቃወም የሚደረጉ ሰልፎች ቀጥለዋል። በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ረቡእ እለት በኢትዮጵያ ኢምባሲ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የሳውዲን ንጉስ ፎቶ ግራፍ አቃጥለዋል። ሀሙስ እለት ደግሞ በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማድሪድ በሚገኘው የሳወዲ ኢምባሲ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ኢትዮጵያውያኑ አቤቱታቸውን ለሳውዲ ኢምባሲ ተወካይ ማቅረባቸውም ታውቋል;፡