ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)
በቅርቡ በአንድ የሳውዲ አረቢያ ህጻን ላይ ግድያን ፈጽማለች ተብላ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባት ኢትዮጵያዊት ሰኞ በመቅላት ድርጊት የሞት ቅጣት እንደተፈጸመባት የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ገለጹ።
በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያዊት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኒታ የአሰሪዎቿን ታዳጊ ህጻን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሏን የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የአገሪቱ ፍ/ቤት በተከሳሿ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔን ቢያስተላልፍም፣ ኢትዮጵያዊቷ ግድያውን በምን ምክንያት እንደፈጸመች የታወቀና የተገለጸ ነገር አለመኖሩን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከሃገሪቱ ዘግቧል።
የሳውዲ አረቢያ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያዊቷ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይቀር ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ የመቅላቱ ድርጊት እንደተፈጸመባት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሳውዲ አረቢያ ሰኞ በኢትዮጵያዊቷ ላይ የፈጸመችውን የመቅላት ድርጊት ጨምሮ በተያዘው የፈረንጆች አመት ብቻ 124 ሰዎችን በተመሳሳይ ድርጊት መግደሏን አዣንስ ፍራስን ፕሬስ በዘገባው አስፍሯል።
በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ በአብዛኛው በቤት ሰራተኝነትና በሌሎች ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።