ኢሳት (ግንቦት 21: 2009)
በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው ከ700 መቶ ሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ አለመታወቁ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳውዲ አረቢያ ያለፈቃድ ይኖሩ የነበሩ 40ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የመውጫ ቪዛ አግኝተዋል ቢልም፣ ሌሎች ከ700 ሺ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ለማወቅ ተችሏል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ቢመለሱ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል ባላወቁበት ሁኔታ ሳውዲ አረቢያን ለቀው ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተመልክቷል። ሆኖም፣ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እስከ ሰኔ 21 2009 ቀን አም ከሳውዲ አረቢያ የማይወጡ ከሆነ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ አንግልቶች ሊደርስባቸው እንደሚችል የስደተኞች ድርጅትን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል። ሳውዲ አረቢያ ያስመቀመጠችው የጊዜ ግደብ ሊጠናቀቅ ወደ አንድ ወር አካባቢ ቢቀረውም፣ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ዜጎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተመልቷል።
በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ዜጎች አገር ለቀው በመሰደድ በአረብ አገራት በጉልበት ስራ ላይ እንዲሰማሩ እንዳደረጋቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚህ በፊት በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ዜጎቹ ላይ እንግልት፣ ግድያ እና አስገድዶ መደፈር ሲደርስባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ምንም አይነት ዕርምጃም ሆነ ተቃውሞ ባለማቅረቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች እንደገለጹት፣ ከመንግስት ምንም አይነት እርዳታ አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።