በሳኡዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ወረቀት ከሌላቸው 400 ሺህ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ወደ ሀገራቸው የተመለሱት 60 ሺህ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘገበ።

ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሪያድ ባለፈው መጋቢት ወር ህጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሯን እንዲለቅቁ የሰጠችው ማስጠንቀቂያና የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀው ትናንትና ነው።
በተጠቀሰው ጊዜ የበርካታ ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ቢሆንም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ባለመፈለጋቸው ዛሬ በሳኡዲ አረቢያ መንግስት ተጨማሪ የአንድ ወር የምህረት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያውያኑ በተከታዮቹ 30 ቀናት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ የሀገራቸው መንግስት ጥሪ ማቅረቡን የዜና አውታሩ አስነብቧል።
የምህረት ጊዜው በአንድ ወር ቢራዘምም 400ሺህ ከሚደርሱ ወረቀት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሦስት ወራት ወይም 90 ቀናት በብዙ ግፊት ወደ ሀገራቸው የተመለሱት 60 ሺህ ብቻ ናቸው።
ከዚህ አንጻር 340 ሺህ የሚሆኑት ቀሪዎቹ ስደተኞች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይመለሳሉ ተብሎ አይጠበቅም። በሳኡዲ አረቢያ ህጋዊ ወረቀት ሳይኖራቸው ከሚሠሩ የውጭ ሀገራት ስደተኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር አላቸው።
እነዚህ ህጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች በተቀመጠላቸው ጊዜ ካልተመለሱ በግዳጅ መጠረዝ ወይም ወህኒ ይጠብቃቸዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ በስደት የሚመጣባቸውን ቅጣት መቀበል ይመርጣሉ።
በጦርነት እየፈራረሰች ባለችው የመን ሳይቀር እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን የስቃይና የሞት ጽዋ እየተጎነጩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ህይወታቸውን ለአደጋ ሰጥተውና ሞትን መርጠው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሰንአ የሚሻገሩ ኢትዮጵያውያን ጥቂት እንዳልሆኑ የዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ያሳያል።
ኢትዮጵያውያን ሞትን እስኪመርጡ እስከዚህ ድረስ ሀገራቸውን የጠሉበት ምክንያት ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።