ጥቅምት ፳፫ (ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት በታጭ አርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ኩርቢና ገነት በሚባለው አካባቢ ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ታጣቂ ሃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት የኢህአዴግ ንብረት የሆነውን ዳሸን ቢራ ጭኖ ይጓዝ የነበረ አንድ ኤፍ ኤስ አር መኪና መጠጥ እንደጫነ አቃጥለውታል። ሌላም ከ35-45 የሚሆን ህዝብ የጫነ አንድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ እና አንድ ሚኒባስም ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ሁለቱም መኪኖች ተቃጥለዋል። መኪኖችን ከሚያጅቡ ወታደሮች ጋር በተደረገ የተኩስ ለውውጥ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሎአል።
በአካባቢው በርካታ የነጻነት ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ከእነዚህ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያድርግ ቆይቷል። ጥቃቱ እንደተሰማ ተጨማሪ ሃይል ወደ አካባቢው ተጉዟል። ገዢው ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገሪቱን አረጋግቷል በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ቢሰጥም፣ ተቃውሞው ከሰላማዊ ወደ አመጽና የመሳሪያ ትግል እየተለወጠ መሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጢስ አባይ የሚገኙ አርሶአደሮች ያለፉትን 2 ሳምንት ከወታደሮች ጋር በምሽት ሲታኮሱ ያሳለፉ ሲሆን፣ ትናንት አቶ ምክሩ ብርሃኑ የተባሉ የጎበዝ አለቃ አንድ የፌደራል ፖሊስ ገድለውና ሁለት ወታደሮችን አቁስለው በመጨረሻም ተገድለዋል። አቶ ምክሩ ከወታደሮች ጋር ለረጅም ሰአታት መዋጋታቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። የአካባቢው ወጣቶችን ለመያዝ ዛሬም ድረስ የቀጠለው እንቅስቃሴ አብዛኞቹ ወጣቶች ውሎአቸውን ጫካ አድርገዋል ወይም ወደ ሌሎች ከተሞች ተሰደዋል። በአካባቢው ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ከፍኖተሰላም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችም የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው ራሳቸውን በመከላከል ላይ ናቸው። በጃዊ ደግሞ የአካባቢው አርሶአደር ታጣቂዎች በመንግስት ወታደሮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በዛሬው እለት ታጣቂ ሃይሎችን በገንዘብ ይረዳሉ የተባሉ 37 የመንግስት ሰራተኞችና ባለሃብቶች ከተለያዩ አካባቢዎች እየተያዙ ታስረዋል።
በባህርዳርም ቀበሌ 3 በባለሰልጣናቱ ሰፈር ቦንብ ፈንድቷል። በፍንዳታው የተጎዳ ሰው ይኑር አይኑር አልታወቀም። በአንዳንሳም አካባቢ እንዲሁ አለመረጋጋት መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል።
በባህርዳር ከተማ ደግሞ የታሰሩ ወገኖቻቸውን ችሎት በመከታተል ላይ የነበሩ ከ 100 በላይ የቀበሌ 05 ወጣቶች ፍርድ ቤት ላይ ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። ከታሰሩት መካከል አንዳንዶቹ ለ1 ወር ታስረው በ5 ሺ ብር ዋስ የተለቀቁ ናቸው። ወጣቶቹ በ3 የተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው እንደሚገኙም ታውቋል። በከተማ ውስጥ ሁለትና ሶስት ሆኖ በፈለገው ቦታ ቆሞ መነጋገር አስቸጋሪ መሆኑንም ወጣቶቹ ለኢሳት ገልጸዋል።
በቆላ ድባም እንዲሁ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች መታሰራቸውን ከአካባቢው የደረሰን ዜና ያመለክታል።