በሳምንት ውስጥ 2 ታሳሪዎች በቂሊንጦ እስርቤት ሞቱ

ኢሳት (ጥር 6 ፥ 2008)

አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙባረክ ይመር እና ጉደታ ኦላንሳ የተባሉ ኢትዮጵያውያን በቂሊንጦ እስርቤት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መሞታቸው ተነገረ።

ከድምጻችን ይሰማ የኢትዮጵያ ሙዝሊም እንቅስቃሴ እነ እንድሪስ መሃመድ መዝገብ ጋር በተያያዘ ከወሎ የታሰረው 9ኛ ተከሳሽ ሙባረክ ይመር መሞቱ ታውቋል።

በአዲስ አበባ በመስራቅ አቅጣጫ ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቂሊንጦ እስር ቤት ከሁለት አመታት በላይ በእስር የቆየው ሙባረክ ይመር፣ ድንገት ታመመ ተብሎ ወደ ህክምና ሲሄድ እንደሞተ ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታም በመጋቢት ወር 2006 አም በተነሳው የመሬት ተቃውሞ ተሳትፏል ተብሎ ከታሰረ በኋላ በዋስ የተፈታው አብደታ ኦላንሳ በምርጫ 2007 ወቅት ለእስር ተዳርጎ ላለፉት 8 ወራት በቂሊንጦ እስር ቤት ያለፍርድ ቢቆይም በዚሁ ሳምንት ተገድሎ የቀብር ስነስርዓቱ በአምቦ ተፈጽሟል።

ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ፣ እና የቀድሞ የኦህኮ አባል መሃመድ አህመድ በተመሳሳይ በእስር ቤት መሞታቸው ታውቋል።

አብደላ ኦላንሳን ለመቅበር የአምቦ ነዋሪ እንዳይወጣ በመከላከያ ሰራዊት ክልከላ ቢደረግም ህዝቡ በነቂስ በመውጣት የተቃውሞ ድምፅ ጭምር እንዳሰማ ታውቋል። በዚሁ የተነሳ የአጋዚ ጦር በወሰደው የሃይል እርምጃ ሌንጮ ዲንቄሳ የተባለ ሰው ጭንቅላቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል።

የከተማው ነዋሪዎች አምቦ ከተማ ወታደራዊ ከተማ ሆናለች ይላሉ። የከተማው ፖሊሶችም እንደነዋሪው ሁሉ ድብደባና እንግልት እየተፈጸመባቸው ለኢሳት ገልጸዋል።

በአምቦ ዩንቨርስቲ ለተማሪዎች የሚደረገውን ተቃውሞ ለመግታት የፌዴራል ፖሊሶች በተማሪዎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ ሲፈጽሙ ታይተዋል። በሃረርጌ መሰላ ወረዳ በሪ ሰዒድ ዓሊ የተባለ ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ ተፈጽሞበት አስከሬኑ ተጥሎ ተገኝቷል። በተመሳሳይ መልኩም በሃረርጌ በግብርና የሚተዳደር ጫላ መሃመድ የተባለ ኢትዮጵያዊ ተገድሎ የቀብር ስነስርዓት የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ነው።

በቄለም ወለጋ የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኑር አህመድ ሳቢት በጥይት እግራቸው ቆስሎ በህክምና የሚድን ባለመሆኑ እግራቸው እንዲቆረጥ ተደርጓል።

በኦሮሚያ ክልል ያለው የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ በድሬዳዋ፣ በምዕራብ ሸዋ ጅባት ወረዳ፣ በሃረርጌ በደኖ፣ እና በአምቦ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢትዮጵያውያን በዋሽንግተን ዲሲ የፊታችን እኤእ ጃንዋሪ 25, 2016 ለሚያካሄዱት አለም አቀፍ ተቃውሞ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል። በዚሁ ሰልፍ ሁሉም ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲገኝ ጥሪ ቀርቧል።