በሳምንቱ መጨረሻ በአሜሪካና አውሮፓ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ

ነሃሴ  ፲፮ ( አሥራ  ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአሜሪካ በኮለራዶ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ  በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያ በጽኑ አውግዘዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደ ላለው ትግልም ድጋፋቸውን ገልጸዋል

ኢትዮጵያውያኑ የአሜሪካ መንግስት በስርኣቱ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። በስፍራው ተገኝተው ለኢትዮጵያውያን ጥያቄ መልስ የሰጡት የምክር ቤት አባሉ ማይክ ሆፍማን ኢትዮጵያ ውስጥ እየጠፈጸመ ያለውን ግድያ አውግዘዋል። ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ናት ያሉት ባለስልጣኑ፣ ጉዳዩን በአሜሪካ ለኢትዮጵያ አምባሳደር እንደሚያሳውቁ፣ እርሳቸው ከምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን ግድያው በአፋጣኝ እንዲቆም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ግድያውን እንዲያጣራ እንዲሁም ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እንደሚሰሩ ተናግረዋል

የስራቸውን ሂደት በየጊዜው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚገልጹም ባለስልጣኑ ቃል ገብተዋል። በተያያዘ ዜና የአሸንዳን በአል ለማክበር በሚል የህወሃት አባላት በአምስተርዳም ያዘጋጁትን የፌሽታ ዝግጅት በኔዘርላንድስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቃውመውታል።

ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት ዜጎች እየተገደሉ በዜጎች አስከሬን ላይ መጨፈር ከባህል አንጻር ተቀባይነት የሌለው፣ በፍጹም ኢትዮጵያውያን የማይወክል አስጸያፊ ድርጊት ነው በማለት የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ፎቶግራፎች ከፍ አድርገው በማሳየት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆነው ተቃውሞአቸውን የገለጹት ኢትዮጵያውያን፣ “አንድ ነን፣ አንለያይም፣ የህወሃት አገዛዝ ይብቃ”  የሚሉ እና ሌሎችንም በርካታ መፈክሮች በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ አሰምተዋል።

ጸባችን ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን ከወያኔ ጋር ነው ያሉት ኢትዮጵያውያን ፣ ወያኔ የትግራይን ህዝብ የማይወክል በመሆኑ፣ የትግራይ ህዝብ ይህን አውቆ ከነጻነት ትግሉ ጋር ይሰለፍ ብለዋል።