በሲጃራ ሙስና የተጠረጠሩት የትንባሆ ሞኖፖል ኃላፊ ነፃ መባላቸውን የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ተቃወመ።

ሐምሌ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፀረ-ሙስና ኮሚሽን- የብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅት የሥራ ኃላፊ በተጠረጠሩበት የእምነት ማጉደል ወንጀል በፍርድ ቤት በነፃ መሰናበታቸውን በመቃወም- ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታወቀ።

ሪፖርተር እንደዘገበው ፤የብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅት ያለቀላቸው ምርቶች ግምጃ ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ በሻና 787,531.50 ሳንቲም በሚያወጣ 210 ካርቶን ኒያላ ሲጋራ በመሰወር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፡፡

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ምድብ ችሎት ባለፈው ሐሙስ ተከሳሹን በነፃ አሰናብቶአቸዋል፡፡

የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የግለሰቡን በነፃ መሰናበት ያላመነበት በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስታውቋል፡፡

ከተጠቀሰው ሲጋራ መሰወር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት የመሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊ በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩ ጥያቄ ያቀረበው ትንባሆ ሞኖፖል ነው፡፡

ድርጅቱ ከመሥሪያ ቤቱ የቀን ሠራተኞች ጥቆማ በሚቀበልበት ጊዜ  የግምጃ ቤት ኃላፊው- ከተደረደሩ ሲጋራዎች መካከል 210 ካርቶን ኒያላ ሲጋራ በተቀነባበረ ስርቆት መጥፋቱን ለሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ሪፖርት አድርገው ነበር፡፡

በዚህ መሠረት ትንባሆ ሞኖፖል በውስጥ ኦዲት ሲጋራ መጥፋቱ እንዲጣራ በማድረግ በማረጋገጡ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩ እንዲጣራ ጥያቄ ያቀርባል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ተጨማሪ መረጃዎችን  ካሰባሰበና የፎረንሲክ ምርመራ በመጋዘኑ ላይ ካደረገ በኋላ ክስ መሥርቷል፡፡

የኮሚሽኑ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በፎረንሲክ መረጃው ሲጋራ የተቀመጠበት  የመጋዘን በር አለመሰበሩንና  በሌላ ቁልፍም አለመከፈቱን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ለተፈጠረው የኒያላ ሲጋራ ጉድለት በቀጥታ ንብረቱን በኃላፊነት የተረከቡት የግምጃ ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ላይ ክስ እንዲመሠረት አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ በጉዳዩ ዙርያ ሊኖር የሚገባው ዝርዝር የምርመራ ሒደት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለተፈጠረው ጉድለት ንብረቱን በኃላፊነት የተረከቡት የግምጃ ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ የመጀመርያው ተጠያቂ በመሆናቸው አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ ትንባሆ ድርጅቱ ጠይቆ ነበር፡፡

ነገር ግን ክሱን ሲከታተል የቆየው ፍርድ ቤት በሌላ ኃላፊ ዘንድም ቁልፍ ስለሚገኝ፣ ግለሰቡን ተጠያቂ ማድረግ እንደማይቻል በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጓል፡፡