በሲያትል እና አካባቢዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የህወሀትን የዘረኝነት አሠራርን አጥብቀው ተቃወሙ

ነሀሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሲያትል እና አካባቢዋ የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ህወሀትን አጥብቀው የተቃወሙት፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ነገ እሁድ  ኦገስት 19 ቀን  በ3515 ሳውዝ አላስካ በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ  በሚካሄድ እና  ከ2 ሰ ዓት እስከ 6 ሰዓት በሚቆይ የመንግስት ስብሰባ ላይ የትግራይ ተወላጆች ብቻ እንዲገኙ ተለይቶ ጥሪ በመደረጉ ነው።

በበርሀ ስማቸው ተወልደ አጋመ ተብለው በሚጠሩት በአምባሳደር ተወልደ ገብሩ እና በትግራይ ክልል የፍትህ ቢሮ ሀላፊ በአቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ በሚመራውና በወቅቱ  የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኩራል በተባለው ስብሰባ  ከትግራይ ተወላጆች በስተቀር አንድም የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ አለመጠራቱ ነው- በሲያትል የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆች ያስቆጣቸው።

የትግራይ ተወላጆቹ፦”ህወሀት ለዘላለም አይኖርም!”በሚል ርዕስ ያወጡትን የአቋም መግለጫ የጀመሩት፦”ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅም እናገር ነበር። እንደ ልጅም አስብ ነበር።እንደ ልጅም እቆጠር ነበር።ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬያለሁ” በሚለው የመጽሐፍ ቃል ነው።

በመግለጫቸው፦“ህወሀት ከተመሰረተ ጀምሮ የትግራይንና የኢትዮጵያን ህዝብ ገድሏል” ያሉት የትግራይ ተወላጆቹ፤”ምናልባት  <የህወሀት መሪዎች ጥፋት ያጠፉት፤ ልጆች ስለነበሩ ነው> የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ።እነሆ ዛሬም ግን ህወሀት  በዕድሜ ሸምግሎ ከጥፋቱ አልተማረም።”በማለት ይህ ጥፋት ማቆሚያው መቼ ? እንደሚሆን በአፅንኦት ጠይቀዋል።

“ህወሀት/ኢህአዴግ ለዘላለም አይኖርም!አገራችን ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ትኖራለች፤ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል።አባቶቻችን ጠብቀው ያስረቡንን አገራችንን ፤እኛም ለተተኪው ትውልድ በአደራ ማስረከብ አለብን። ይህን ሳንችል ስንቀር ግን መጪው ትውልድ ይወቅሰናል”ብለዋል-የትግራይ ተወላጆቹ።

“ከትውልድ ወቀሳ ለመዳን፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር በመሆን የተበላሸውን እያደስን እና የጎበጠውን እያቃናን መኖር ሲገባን፤እኛ የትግራይ ተወላጆች ግን ይህን ከአባቶቻችን የወረስነውን ታሪክ ዘንግተናል”ያሉት በሲያትል እና አካባቢዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፤ይህን ለማለት ያስገደዳቸውም፤  በሲያትል በሚደረገውና  በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሚመክረው ስብሰባ ላይ፤ የትግራይ ተወላጆች ብቻ መጠራታቸውን ስለደረሱበት እንደሆነ አብራርተዋል።

የትግራይ ተወላጆቹ  በመጨረሻም በስብሰባው ለመሳተፍ ላሰቡት ሰዎች  ባስተላለፉት መልዕክት፦”ህወሀትንም ሆነ ኢህአዴግን እንደ ቋሚ መንግስት ቆጥራችሁና ዛሬም እንደ ትናንቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተለይታችሁ ለብቻችሁ ለመሰብሰብ ማቀዳችሁ አሳዝኖናል።ከዚህ ዓይነት ጥፋት ታቅባችሁ እና ካለፈው ስህተት ታርማችሁ ለአንዲት ኢትዮጵያ ትታገሉ ዘንድ በሰፊው ትግራይ ህዝብ ስም እናሣስባችሁዋለን!”ብለዋል።

ስብሰባውን ከሚመሩት አንድኛውና የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፦በምርጫ 97 ወቅት ኢህአዴግ በምርጫ መሸነፉን ተከትሎ በጀርመን ራዲዮ የአማርኛው ፕሮግራም በመቅረብ፦”ትግሬን ወደ መቀሌ፤ንብረቱን ወደ ቀበሌ እየተባለ ነው” በማለት፤  በኢትዮጵያ ህዝብ ሊፈፀም ቀርቶ ሊታሰብ የማይችልን  እጅግ ዘግናኝ እና ለሚዲያ ፍጆታ የማይበቃን አደገኛ የዘረኝነት ቅስቀሳ ማሰራጨታቸው  አይዘነጋም።

የሲያትሎቹ የትግራይ ተወላጆች፦“ከእንግዲህ ግን የትግራይን ህዝብ ከሌላው ወንድሙና እህቱ ጋር በማጋጨት የሥልጣን ዕድሜን የማራዘሙ ፀያፍ ፖለቲካ  ማክተም አለበት”ነው የሚሉት። ቀደም ሲል ባለማወቅም ሆነ እውነታውን ባለመረዳት የህወሀትን መንገድ የደገፉ ሁሉ፤ አዲስ የአስተሣሰብ ለውጥ ሊያደርጉ እና በአዲስ አገራዊ ሀሳብ ዳግም ሊወለዱ እንደሚገባቸው በመጠቆም።

ለዚህም ነው፦”ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅም እናገር ነበር። እንደ ልጅም አስብ ነበር።እንደ ልጅም እቆጠር ነበር።ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬያለሁ” በማለት በመግለጫቸው መግቢያ ላይ ስለ አስተሣሰብ ዕድገትና ለውጥ የሚያመላክተውን የመጽሐፍ ቃል ያሰፈሩት።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide