በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሱዳን ፖሊሶች ጥቃት ተፈጸመባቸው አንድ ኢትዮጵያዊም ተገሏል

የካቲት ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪነታቸው በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ የሆነ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በኤንባሲው ቅጽር ግቢ በመገኘት መብታቸውን በመጠየቃቸው በኢትዮጵያ ኤንባሲ ትእዛዝ ሰጭነት በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ጥቃት ተፈጸመባቸው። ባለፈው ሳምንት ከኤንባሲው ጋር ለመነጋገር በያዙት ቀነ ቀጠሮ መሰረት ወደ ኤንባሲው የሄዱ ቁጥራቸው ከ2 ሽህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በስፍራው ሲደርሱ በወታደራዊ ተሽከርካሪ ተጭነው የመጡ ሱዳናዊያን ታጣቂዎች ስደተኞቹን በጭካኔ በመደብደብ አካላዊ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። ከመሃከላቸውም አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛም በስለት ተወግቶ ተገሏል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በጭካኔ ተደብድበው በሁለት አይሱዙ መኪና ተጭነው ወደ እስር ቤት ተግዘዋል። የተወሰኑ ቁስለኞች ወደ ሆስፒታን ተወስደዋል። በሱዳን ኢትዮጵያዊያኑ ከህግ አግባብ ውጪ የመብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው ኤንባሲው ከለላ አይሰጥም። ከአምስት ሺ በላይ እንዲከፍሉ መገደዳቸውንም ይናገራሉ።